በዕለቱ የመጀመሪያ በነበረው እና ባህርዳር ከተማ የወላይታ ድቻን ያለመሸነፍ ግስጋሴን ከገባተበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ
የተለወጠው ባህር ዳርን ስለመመልከታችን
”በሁለቱ ጨዋታዎች ሙሉ ለሙሉ የኔ የሆነውን ሞዴል አይተናል ማለት ትንሽ ይከብዳል። መስራት ያሉብን ስራዎች አሉ። እንደተመለከትከው በኳስ ቁጥጥር ላይ አተኩረን ነው የምንጫወተው። ለዚህ ደግሞ ሜዳው አመቺ መሆን አለበት። ያ ስላልሆነ ከሽነፈቶቻችን በኋላ ስትራቴጂያችን ቀይረን ነው የመጣነው። በዚህም በሁለቱ ጨዋታዎች ውጤታማ ሆነናል። ዞሮ ዞሮ ግን ሜዳው በሚፈቅደው የምንችለውን አድርገን ወደ ምንፈልገው አጨዋወት እየመጣን ነው ብዬ አስባለሁ።”
ሰለቡድኑ የዕለቱ የጨዋታ እንቅስቃሴ
“በመጀመሪያ አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ ብልጫ ነበረን የግብ እድሎችን መፍጠር ችለናል ነገርግ መጨረሻ ላይ የተቆጠረችብን ግብ በስነልቦና ረገድ ልጆቹን የጎዳች ነበረች ውጤቱን ለማስጠበቅ ልጆቹ ብዙ ሲሸሹ ነበር ነገርግን ሶስተኛውን ግብ ካስቆጠርን በኃላ በተወሰኑ መሻሻሎች ግን ነበሩ።”
በጨዋታው ይዘውት ስለገቡት አቀራረብ
“ሁለቱ አጥቂዎች ፊት ላይ በሚቀሩበት ጊዜ የእነሱ አራት ተከላካዮች ወደ ኃላ ይቀሩ ነበር በዚህም ፍፁም የተሻለ መንቀሳቀሻ ቦታ እንዲያገኝ አስችሎታል ፍፁም በእስካሁኖቹ ጨዋታዎች ያገኛቸውን እድሎች መጠቀም አለመቻሉ እንጂ ብዙ እድሎችን ፈጥሯል።ዛሬም አላማችን የነበረው ይህን እንዲያደርግ ነበር እሱንም ማድረግ ችሏል።”
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ
ሊጉን ስለመምራት
“በግልፅ ለመናገር የእኛ ስብስብ ሊጉን ለማሸነፍ የተሰራ አይደለም ፤ በአጋጣሚ በሚገኙ ውጤቶች ነጥባችንን አስጠብቀን መጥተናል ነገርግን ብዙ የሚቀሩን ነገሮች አሉ ዛሬም ብልጫ የተወሰደብን ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረጉ ሽግግሮች የተሻለ ስለነበሩ ብልጫ ተወስዶብናል።”
ስለተቆጠሩባቸው ፈጣን ሁለት ግቦች
“ያልተጠበቁ ግቦች ስላስተናገድን በተጫዋቾቻችን ዘንድ መቀዛቀዝ ፈጥረው ነበር ነገርግን ተጫዋቾቼ ባላቸው አቅም የሚችሉትን ለማድረግ ሞክረዋል በዚህም የተወሰኑ ዕድሎችን ብንፈጥርም መጠቀም አልቻልንም ይህም ለቀጣይ ጠንክረን እንድንሰራ ያደርገናል።”
ስለተጋለጠው የተከላካይ መስመራቸው
“ተከላካዮች ብቻ ሳይሆን ዛሬ የመከላከል አደረጃጀታችንም ጥሩ አልነበረም ከአማካዮቻችን የተነጠቁ ኳሶች ነበር የተቆጠሩብን ግለሰባዊ ስህተቶች ይመስላሉ እንጂ በመስመሮች መካከል የነበረው ክፍተት ዋጋ አስከፍሎናል።”