ሀዲያ ሆሳዕና ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ በሀብታሙ ታደሰ ሁለት ግቦች ታግዞ የዓመቱን የመጀመሪያ ድል መከላከያን በማሸነፍ አስመዝግቧል።
በኢትዮጵያ ቡና ተረተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት መከላከያዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ዓለምአንተ ካሳ እና ቢኒያም ላንቃሞ በደሳለኝ ደባሽ እና ኤርሚያስ ኃይሉ ተተክተዋል። በተመሳሳይ ከሽንፈት መልስ የመጡት ሀዲያዎችም በአዲስ አበባ ከተረቱበት ፍልሚያ ዑመድ ኡኩሪን በባዬ ገዛኸኝ፣ መላኩ ወልዴን በሄኖክ አርፊጮ እንዲሁም ፍቅረየሱስን ተወልደብርሃንን በኤፍሬም ዘካሪያስ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።
በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ናቸው። በዚህም ከወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ የተገኘው የቅጣት ምት ሲመታ ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ ነበር። በዘጠነኛው ደቂቃ ደግሞ በተመሳሳይ ሄኖክ በተቃራኒ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ ከግብ ጋር ከማገናኘት ቢዳዳም ለጥቂት ወጥቶበታል። መከላከያዎችም የቆመ እና ተሻጋሪን ኳስ ለቁመታሙ አጥቂያቸው ኦኩቱ ኢማኑኤል እየላኩ ቀዳሚ ለመሆን ተንቀሳቅሰዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቢኒያም በላይ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ፍጥነቱን ተጠቅሞ የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ ነበር።
አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ሀዲያዎች ከወትሪው በተለየ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥሩ ነበር። በ17ኛው ደቂቃም ባዬ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ክሌመንትን ፈትነው ተመልሰዋል። ከአምስት ደቂዎች በኋላ ግን የመከላከያን የግብ ክልል ፈትሸው አፍረው አልተመለሱም። በዚህም የግራ ተመላላሹ ኢያሱ ታምሩ ፈጣን ሩጫ በማረግ ሲፈነጠር ጉዳት አስተናግዶ ሜዳ ላይ የወደቀውን ገናናውን በማለፍ ወደ ሳጥን የላከውን የመሬት ለመሬት ኳስ በሩቁ ቋሚ የነበረው ሀብታሙ ታደሰ አግኝቶት ግብ አድርጎታል።
ግቡ ከተቆጠረ በኋላ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ሌላ የጠራ የግብ ዕድል ማስተናገድ ያልቻለው ጨዋታው መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ እና ቶሎ ቶሎ መቆራረጥ የበዛበት እንቅስቃሴ ማስመልለት ይዟል። ረጃጅም ኳሶች በርከት ብለው ቢታዩም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር አጋማሹ በሀዲያ ሆሳዕና አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
የመከላከያው አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በቶሎ ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ የመከላከል ባህሪ ያለው ተጫዋች አስወጥተው የማጥቃት ባህሪ አስገብተዋል። ይህ ቢሆንም ግን እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ የሰላ ጥቃት ሀዲያ ላይ ሳይፈፅሙ ጨዋታው ቀጥሏል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ አጋማሹ ሲጀመር ደሳለኝ ደባሽን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ገዛኸኝ ባልጉዳ ከርቀት ጥብቅ ኳስ የመታ ቢሆንም ኳሱ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።
ለዐይን ማራኪ ያልነበረው ጨዋታው በ79ኛው ደቂቃ ላይ በሌላ የቆመ ኳስ ግብ ሊያገኝ ተቃርቦ ነበር። በዚህም ቢኒያም በላይ ጥፋት ሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት ባዬ አክርሮ የመታው ቢሆንም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ስምንት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ሀዲያ መሪነቱን ወደ ሁለት አሳድጓል። በዚህም ከርቀት የተመታውን ኳስ ኢያሱ በተከላካይ መሐል ለሀብታሙ አመቻችቶለት ሀብታሙ ጎል አድርጎታል። ከሁለተኛው ጎል በኋላ መከላከያዎች ጎል ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮ ወደ ጨዋታው የመመለስ ጥረታቸው ሳይሰምር ቀርቷል።
ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ የመከላከያው የመስመር ተከላካይ ዳዊት ማሞ በሀብታሙ ታደሰ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ (ቀድሞ 46ኛው ደቂቃ ላይ አይቶ ነበር) ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ሀዲያ ሆሳዕና የነበረው ሦስት ነጥብ ላይ ሌላ ሦስት ነጥብ አክሎ ያለበትን ደረጃ ለሰበታ ከተማ በጊዜያዊነት አስረክቦ ወደ አስራ አራተኛ ከፍ ሲል መከላከያ ደግሞ በአስር ነጥቦች ያለበት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ረግቶ ተቀምጧል።