የሦስተኛውን የጨዋታ ዕለት ሁለተኛ ግጥሚያ የተመለከተው ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።
በመካከለላቸው ልዩነቶች ቢኖሩም የሁለቱ ቡድኖች አጀማመር እንደፍላጎታቸው አልሆነም። የተሻለ ውጤት ያለው ሀዋሳ ከተማ ከሦስት ጨዋታዎች ሁለት ድል አስመዝግቦ ዓመቱን ቢጀምርም የመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግን ከሁለት ነጥብ በላይ አላስገኙለትም። ሰበታ ከተማ ደግሞ ከዚህ በባሰ ሁኔታ እስካሁን ከድል ጋር ያልተገናኘ ሲሆን እጁ ላይ ያሉት አራት ነጥቦች በሙሉ ከአቻ የተገኙ ናቸው። ይህንን ስናስብ የነገውን ጨዋታ አሸንፎ ሦስት ነጥብ ማሳካት ለቡድኖቹ ወቅታዊ ሁኔታ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን እንገነዘባለን።
የሁለቱ ተጋጣሚዎች የማጥቃት ዕቅዶች በቅርብ ሳምንታት ላይ ያሳዩት አፈፃፀም የነገው ጨዋታ ከሙከራዎች የራቀ እንዳይሆን ያሰጋል። በአመዛኙ የሦስትዮሽ የአጥቂ መስመሩ ላይ ዕምነቱን የጣለው ሀዋሳ ከተማ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ጠንቀቅ ማለት ከመምረጡ ጋር ሊያያዝ ቢችልም በማጥቃት ወረዳው ላይ በቂ ተሰላፊዎቹን ሲያደርስ አይታይም ነበር። ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ባህሪን ተላብሶ በታየባቸው ቅፅበቶችም ረዘም ያሉ ኳሶችን ይጥልበት የነበረው መንገድ የጨዋታው ግለት የፈጠረው እንጂ ሁለተኛ ዕቅዱ ነበር ለማለት አያስደፍርም። ሰበታ ከተማም እንዲሁ የሚያጠቃበት መንገድ እጅግ ደካማ ነበር። ለፊት አጥቂው ፍፁም ገብረማሪያም የሚደርሱ ኳሶች በቁጥርም በጥራትም እየቀነሱ እየሄዱ ናቸው። እንደነገ ተጋጣሚው ሁሉ ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶቹን የሚጠቀምበትም መንገድ አጥጋቢ ሊሆን አልቻለም።
ዕድሎችን ከመፍጠር ችግራቸው ባለፈ ሁለቱም ጋር የአጨራረስ ችግሮች መኖራቸው አይካድም። ሆኖም የአማካይ መስመራቸውን ይበልጥ አጎልብቶ መግባት እና የዕድሎችን ቁጥር ማብዛት አጥቂዎችን ከተደጋጋሚ ዕድሎች ውጤታማ ለማድረግ በር ሊከፍት ይችላል። ከዚህ አንፃር ሀዋሳ ከተማ ወንድምአገኝ ኃይሉን ከጉዳት መልስ ማግኘቱ ተጠቃሚ ያደርገዋል። በንፅፅር ከተጋጣሚው የተሻለ አብሮ የቆየ የወገብ በላይ ቡድን መያዙም የተሻለ ዕድል የሚሰጠው ይመስላል። በሰበታ ከተማ በኩል በተለየም ወሳኝ የሆነው የአስር ቁጥር ሚና ላይ ያለው የተጫዋቾች መለዋወጥ የማጥቃት ፍሰቱን ወጥ እንዳይሆን ያደረገው ይመስላል። ከዚህ ይልቅ ለአጥቂነት የቀረቡ ተጫዋቾችን ከዋናው አጥቂ ጀርባ ማሳለፍ ምርጫው ያደረገው ሰበታ ነገ የተሻለ ዕቅድ ይዞ እንዲገባ ይጠበቅበታል።
ከዚህ ውጪ ሰበታ ከተማ በድሬዳዋው ጨዋታ የታየበት የመስመር ጥቃቶችን የመመከት ድክመት ከተደገመ ፈዘዝ ብሎ የከረመው የሀዋሳ ከተማ የፊት መስመር ጥቃት ዳግም የሚደምቅበትን በር ሊከፍት ይችላል። በአንፃሩ በጉዳት እና ቅጣት የሳሳው የሀዋሳ የኋላ ክፍልም አዲስ ጥምረት ለመፍጠር ሊገደድ መቻሉ ለሰበታ የራሱን በጎ ጎን ይዞ ሊመጣ ይችላል። ከሁሉም በላይ ግን ቡድኖቹ ከሰሞኑ ጨዋታዎቻቸው አንፃር እጅግ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ መግባት ብዙ ለውጥ ፈጥረው እንዲውጡ እንደሚረዳቸው ይታመናል።
ሀዋሳ ከተማ ፀጋአብ ዮሐንስ እና አብዱልባሲጥ ከማልን በጉዳት ፀጋሰው ድማሙን ደግሞ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ መጠቀም አይችልም። በሰበታ ከተማ በኩልም መሀመድ አበራ እና አክሊሉ ዋለልኝ አሁንም ጉዳት ላይ ሲሆኑ ወልደአማኑኤል ጌቱ እና ቢያድግልኝ ኤልያስም መጠነኛ ጉዳት ገጥሟቸዋል።
ጨዋታውን ፌደራል ዮናስ ማርቆስ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
ከዚህ ቀደም በስምንት አጋጣሚዎች እርስ በእርስ ሲገናኙ ሰበታ ከተማ አምስቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው። ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ አንድ ጊዜ ብቻ ድል ቀንቶታል። በጨዋታዎቹ ሰበታ ከተማ አስር ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ስድስት ግቦች አሏቸው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
መሀመድ ሙንታሪ
ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ዮሃንስ ሱጌቦ
ወንድማገኝ ኃይሉ – ዳዊት ታደሰ – በቃሉ ገነነ
ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ለዓለም ብርሀኑ
ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ታፈሰ ሰርካ
ክሪዚስቶም ንታንቢ – በኃይሉ ግርማ
ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ – ጁኒያስ ናንጄቤ
ፍፁም ገብረማርያም