አራት ግቦች በተስተናገዱበት የምሽቱ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሰበታ ከተማን ሦስት ለአንድ አሸንፏል።
በስድስተኛ የጨዋታ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ለአንድ ተሸንፈው የነበረው ሀዋሳዎች በፍልሚያው ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ፀጋአብ ዮሐንስን በዮሐንስ ሴጌቦ፣ አብዱልባሲጥ ከማልን በወንድማገኝ ኃይሉ እንዲሁም መድሐኔ ብርሃኔን በዳዊት ታደሰ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ገጥመው ያለ ጎል አቻ የተለያዩት ሰበታ ከተማዎች ደግሞ ጌቱ ሀይለማርያምን በኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ ክሪዚስቶም ንታምቢን በአንተነህ ናደው፣ ፍፁም ገብረማርያምን በዘላለም ኢሳይያስ፣ ቢያድግልኝ ኤሊያስን በዱሬሳ ሹቢሳ እንዲሁም በረከት ሳሙኤልን በጁኒያስ ናንጄቦ በመለወጥ ጨዋታውን ቀርበዋል።
የተመጣጠነ ፉክክር ማስመልለት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ ሲያይበት ነበር። ቡድኖቹም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለማግኘት ሲጥሩ የነበረ ሲሆን ከወትሮው በተለየ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ኖሯቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሰበታዎች ግን በጨዋታ ያደረጉትን የመጀመሪያ የሰላ ጥቃት ፍሬያማ አድርገዋል። በአስረኛው ደቂቃም ከቀኝ መስመር መነሻን ያደረገ ኳስ ወደ ሳጥን ሲጣል በጥሩ ቦታ አጠባበቅ ላይ የነበረው ዱሬሳ ሹቢሳ በሩቁ ቋሚ በመገኘት ኳስ እና መረብን በግንባሩ አገናኝቷል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከሦስት ደቂቃዎች በላይ ያላስፈለጋቸው ሀዋሳዎች ደግሞ ከመሐል የተሻገረን ኳስ ወንድማገኝ ኃይሉ ከተከላካዮች ጀርባ ፈጥኖ በማግኘት ለኤፍሬም አሻሞ አቀብሎታል። ኤፍሬምም በመጀመሪያ የደረሰውን ኳስ በግንባሩ ሲሞክር ምንተስኖት የመለሰበት ሲሆን የተመለሰውን ኳስ ደግሞ በቀኝ እግሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።
ሀዋሳ ከተማዎች የአቻነቱን ግብ ካገኙ በኋላ በደቂቃዎች ልዩነት በመስፍን ታፈሰ እና በቃሉ ገነነ አማካኝነት መሪ ለመሆን ከጫፍ ደርሰው ነበር። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም መሪ ለመሆን ጥረው በ31ኛው ደቂቃ ተሳክቶላቸው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም ቡድኑ በሰበታ ግራ መስመር ላይ ጫና በመፍጠር በዳንኤል ደርቤ አማካኝነት ያሻገረውን ኳስ በሁለቱ የመሐል ተከላካዮች (አንተነህ እና ሳሙኤል) መሐል በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ብሩክ በየነ በነፃነት ኳሱን በግንባሩ ወደግብነት ቀይሮታል። ከመምራት ወደ አቻነት ከዛም ወደ መመራት ያመሩት ሰበታዎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ዳግም አቻ ሊሆኑ ነበር። በዚህም ሳሙኤል ሳሊሶ ከወደ ቀኝ ባደላ ራቅ ካለ ቦታ አክርሮ የመታውን የቅጣት ምት ኳስ ቁመታሙ የግብ ዘብ መሐመድ ሙንታሪ እና የግቡ አግዳሚ ተባብረው ግብ ከመሆን አግደውታል። አጋማሹም ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ተስተውሎበት በሀዋሳ መሪነት ተጠናቋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ሰበታዎች በኋላ መስመራቸው የትኩረት ማነስ እና የመግባባት ችግር ዋጋ ሲከፍሉ የነበረ ሲሆን በሁለተኛውም አጋማሽ ይህንን ችግር መላ ሳይዘይዱለት ገብተው ግብ አስተናግደዋል። በዚህም በ52ኛው ደቂቃ ወንድማገኝ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በቃሉ ሲያሻማው መስፍን ታፈሰ ተጠቅሞበት የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት አሳድጓል።
በእጃቸውን የገባውን ውጤት አሳልፈው የሰጡት ሰበታዎች በ57ኛው ደቂቃ በእንቅርት ላይ አይነት ነገር ገጥሟቸዋል። በዚህም በ45ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ካርድ አይቶ የነበረው የቡድኑ አምበል በረከት ሳሙኤል አስራ አምስት ደቂቃ ሳይሞላው ሁለተኛ ጥፋት ሰርቶ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳው ወጥቷል። ይህንን ተከትሎ የቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ከባዱን ፈተና መጋፈጥ ጀምረው በመልሶ ማጥቃት ቢያንስ አቻ ለመሆን ታትረዋል። በተለይ በ80ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከቅጣት ምት የላከው ኳስ ምናልባት ቡድኑን የሚነሳሳበት ሊሆን የነበረ ቢሆንም ሙንታሪ ተቆጣጥሮታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ የደረሱበትን አጋጣሚ ቢፈጥሩም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው ተደምድሟል።
በውጤቱ መሠረት ከጨዋታው መጀመር በፊት አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ሀዋሳዎች ነጥባቸውን አስር በማድረስ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ እስካሁን አንድም ድል ያላገኘው ሰበታ ከተማ ደግሞ በአራት ነጥቦች አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።