ሀዋሳ ከተማዎች ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኃላ ሰበታ ከተማን በመርታት ወደ አሸናፊነት ከተመለሱበት ጨዋታ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለጨዋታው
“ከዚህ በፊትም እንዳልኩት በእንቅስቃሴ የተሻልን ሆነን ነጥቦችን እያጣን ነበር ዛሬም ይህ ነገር በመጀመሪያው ደቂቃ ተመልክተን ነበር ነገርግን ተመሳሳይ ነገር እንኳን ቢፈጠር ብለን ተነጋግረን ስለነበር መቆጠሩ ብዙም አላስጨነቀንም በእንቅስቃሴ ረገድ ቡድናችን ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት የሚሄድ ስለሆነ ተከላካይ ላይ የምንሰራቸውን ስህተቶችን መቀነስ ነበር የፈለግነው ቡድኑም በወጣቶች የተገነባ ስለሆነ ከጨዋታ ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ነበር ችግራችን ዛሬ ሶስቱም አጥቂዎቻችን ግብ ማስቆጠር ችለዋል ይህ እስከዛሬ ያጣነውን ነገር ፊት ላይ አግኝተናል ማለት ይቻላል።”
አስቀድመው ግብ ስለማስተናገዳቸው
“የልጆቹ ተነሳሽነት ጥሩ ስለነበር አስቀድመው ቢያስቆጥሩብንም ማግባት እንደምንችል ተነጋግረን ነበር እነሱ ዛሬ ይዘው የመጡት ነገር በግራ በኩል ተጫዋች ከመሀል እየወሰዱብን በተደጋጋሚ ክፍተቶችን ለመፈለግ ይመጡብን ነበር ነገርግን ተጫዋቾችን በመቀያየር ያንን ካስተካከልን በኃላ ያንን ቦታ ተቆጣጥረን ነበር።”
ሰበታ በጎዶሎ ልጅ የተሻለ ስለመሆናቸው
“ይህ የተለመደ ነገር በጎዶሎ ስትሆን የሆነው ሆኗል ብለህ ባለህ ነገር ለማጥቃት ነው የምትሞክረው በተቃራኒ ያለው ቡድን ደግሞ ጎዶሎ ናቸው ብሎ በማሰብ ነቅሎ ይወጣል በዚህ ረገድ በጎዶሎ የሚጫወተው ቡድን የተሻለ ሲንቀሳቀስ ተመለከተናል ይህንን ነገር እኛ ከሆሳዕና ጋር ስንጫወት በጎዶሎ ተጫዋቾች የተሻልን ነበርን።በመሆኑም እየመራን ስለነበርን ዋጋ ላለመክፈል በጥንቃቄ ለመጫወት ሞክረናል።”
ስለቡድኑ ደጋፊዎች
“ደጋፊዎቻችን በዚህ አጋጣሚ ለማመስገን እወዳለሁ በሀዲያ ጨዋታ ነጥብ መጣላችን ያልተጠበቀ ስለነበር ከጨዋታው በኃላ አለመግባባቶች ነበሩ ነገርግን ከዛ በኃላ በቅርበት ተነጋግረን ባለፈው ጨዋታ በጊዮርጊስ ተሸንፈን እንኳን እስከመጨረሻው ሲያበረታቱን ነበር ዛሬም እየተመራን ቢሆን ሲጨፍሩ ነበር ይህን ያስቀጥሉ እኛው በውጤት ደረጃ እነሱን ለማስደሰት እንጥራለን።”
ዘላለም ሽፈራው – ሰበታ ከተማ
ሰለ ጨዋታው እና ቀጣይ የቤት ስራዎች
“እንደ አጠቃላይ ቡድናችን ላይ መከላከሉ ላይ ችግር አለ ስትል ጎል ማስቆጠሩ ላይ ችግር አለ በተቃራኒው በጎል የተሻለ ነገር ሲኖር መከላከሉ ደካማ ይሆናል እንደአጠቃላይ ስራ የሚሆነው እንደ ቡድን የተጫዋቾቹን ስነ ልቦና መገንባት ነው ከዚያ በኃላ ምንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ማሳየት ይቻላል። እንደ ቡድን አጠቃላይ ቅርፁን ማሻሻል ይቻላል ይህን ማስተካከል ካልቻልን ግን ነገሮች እየከበዱ ነው የሚሄዱት።”
ጫና ውስጥ ለመሆኑ
“ይህን ጉዳይ በሁለት ነገሮች መመልከት ይገባል አንደኛው የቡድኑን ውጤት በፍጥነት እንዴት ማስተካከል ይቻላል የሚለው ነው ሁለተኛው ደግሞ ከውጤት ጋር በተያያዘ ምንም ነገር ሲሆን የመጀመሪያው ተወቃሽም ተሞጋሽም አሰልጣኙ እንደመሆኑ የምሰጋው ነገር ባይኖርም የምጠረጥራቸው ነገሮች አሉ። ስራ አጣለሁ ብዬ አልሰጋም ነገርግን ሀላፊነቱን ልታጣው እንደምትችል በተወሰነ መልኩ ትጠረጥራለህ። መገለጫው ውጤት እንደመሆኑ ወዲህ ወዲያ ብለህ የምትሸሸው ነገር አይኖርም ስለዚህ እኔ በዚህ መልኩ ነው የማየው።”