አምስት ግቦችን ያስተናገደው የሀዲያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በሀዲያ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሀዲያ ሆሳዕና መከላከያን በረታበት ጨዋታ ጉዳት የገጠማቸው ብርሀኑ በቀለ እና ኤፍሬም ዘሪሁንን ለዛሬ በፀጋዬ ብርሀኑ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ለውጦ ወደ ሜዳ ሲገባ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት አብዱርሀማን ሙባረክን በሙኀዲን ሙሳ ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካተዋል።
የጨዋታው መጀመሪያ አነጋጋሪ የሆኑ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶችን ያሳየን ነበር። በቅድሚያ የዕለቱ አርቢትር ፍሬዘር ካሳ አብዱለጢፍ መሀመድ ላይ የሰራው ጥፋት ሳጥን ውስጥ ነው በማለት ለድሬዳዋ ከተማ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተው አብዱርሀማን ሙባረክ ግብ አድርጎታል። በመቀጠል ከአምስት ደቂቃ በኋላ ፍቅረየሱስ በአብዱለጢፍ ጥፋት ተሰርቶበታል በማለት ለሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁ የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጡ ሄኖክ አርፌጮ ቢመታም ፍሬው ጌታሁን አድኖበታል።
በአጠያያቂዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት ክስተቶች ተጋግሎ የጀመረው ጨዋታ ግን በፍጥነቱ ዝግ እያለ ቀጥሏል። ሁለቱም ኳስ ለመመስረት ጥረት ቢያደርጉም መስመሮችን ለመጥቀም ያደርጉ የነበረው ሙከራ በተደጋጋሚ እየተቆራረጠ የጨዋታ ሂደቱን ለዓይን የማይስብ አድርጎታል። 24ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ ሀዲያዎች ድሬ ሳጥን ውስጥ መገኘት ሲችሉ ቀኝ መስመር ተመላላሹ ፀጋዬ ብርሀኑ ከፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን የደረሰውን ኳስ ከቀኝ ወደ ውስጥ አሳልፎለት ሀብታሙ ታደሰ ወደ ግብ ቢጨርፈውም ፍሬው ጌታሁን አድኖበታል።
ከውሀ ዕረፍት መልስ የመስመር ተመላላሾቻቸውን እያሱ እና ብርሀኑ ቦታ ቀያይረው የገቡት ሆሳዕናዎች ተጭነው ተጫውተዋል። ሆኖም ያደረጓቸው ሙከራዎች የተሻለ የነበረውን የተስፋዬ አለባቸው የ42ኛ ደቂቃ የሳጥን ውጪ ሙከራ ጨምሮ ኢላማቸውን በብዙ ርቀት ያልጠበቁ ነበሩ። ድሬዎች በበኩላቸው ወደ አጋማሹ መገባደጃ ላይ ከሜዳቸው በመውጣት ወደ ግራ ያደሉ ጥቃቶችን መሰንዘር ችለው ነበር። ከዚህ ውጪ አልፎ አልፎ ይታዩ የነበሩ የቆሙ ኳሶችም ውጤታማ ሳይሆኑ አጋማሹ በድሬ መሪነት ተገባዷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ጀምሮ ብዙም ሳይቆይ ሀዲያ ሆስዕናዎች አቻ ሆነዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር በውጪ እግሩ ቆርጦ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ፍቅረየሱስ ሞክሮ በፍሬው ሲመለስበት ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ ግብ አድርጎታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ሳምሶን ጥላሁን ከሀብታሙ ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ከተከላካዮች ጀርባ በጣለው ኳስ ፀጋዬ ከፍሬው ጋር ቢገናኝም በግንባር ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በፍሬው ተይዞበታል።
የድሬዳዋ የማጥቃት መነሳሳት የተከላካይ ክፍሉን ወደ መሀል ሜዳ ማስጠጋቱ ሀዲያዎች ፈጣን ጥቃቶችን ለመሰንዘር ምቹ አድርጎላቸዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይም ሳምሶን በድጋሚ ወደ ፊት የጣለውን ኳስ ሀብታሙ እየነዳ ገብቶ ያደረገው ሙከራ ወደላይ ቢነሳም የድሬዳዋን ይህንን ክፍተት በድጋሚ ያሳየ ነበር። ያም ሆኖ ድሬዎች ለማጥቃት የወሰዱት እርምጃ 62ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። በቀኝ በኩል በእንየው እና አብዱርሀማን ቅብብል ሳጥን ውስጥ ደርሰው እንየው በመጨረሻ በተከላካዮች ችላ ለተባለው አቤል ያደረሰውን ኳስ አቤል ወደ ግብነት በመለወጥ ድሬን በድጋሚ መሪ አድርጓል።
73ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ አጠያያቂ ፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ ከፌደራል ዳኛ ዓለማየሁ ለገሰ ታይቷል። የኤሊያስ አታሮ ረጅም ኳስ ድሬ ሳጥን ውስጥ ሲገባ አውዱ ናፊዩ እና ባዬ ገዛኸኝ ኳስ ለማግኘት ባደረጉት ጥረት ውስጥ ጥፋት ተሰርቷል በማለት የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ሄኖክ አርፊጬ 75ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፎ ቀድሞ የሳተውን ኳስ አካክሷል።
ቀጣዮቹ ደቂቃዎች በሁለቱም ሳጥኖች ጥቃቶች የተመላለሱባቸው ነበሩ። ሆኖም ሆሳዕናዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ የሄኖክ አርፌጮን የማዕዘን ምት ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ ሲሞክር ያሳዩትን ጥረት ደግመው ሦስተኛ ግብ አግኝተዋል። የዚህ ሙከራ ኮፒ የነበረው ሌላኛው የ84ኛ ደቂቃ የማዕዘን ምት በድሬዎች የመከላከል ትኩሩት አናሳነት ታግዞ ግን ግብ ሆኗል። ሀብታሙ ታደሰ የፍሬዘር ካሳን የማዕዘን ምት የግንባር ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ተቆጣጥሮ ሦስተኛ ጎል አድርጎታል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ቶሎ ቶሎ ወደ ሀዲያ ሳጥን ኳሶችን ለማድረስ ጥረዋል። ሆኖም ሁለቴ ከመመራት ተነስተው ቀዳሚ ሆኑት ሀዲያዎች ሌላ ግብ ላለማስተናገድ ያደረጉት ጥረት ሰምሮላቸው ጨዋታው በ 3-2 ውጤት ተጠናቋል።
በውጤቱ ሀዲያ ሆሳዕና ከወራጅ ቀጠና በመውጣት የ14ኝነት ደረጃውን ለድሬዳዋ ከተማ አስረክቦ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።