ነገ ምሽት 12 ሰዓት የሚደረገውን የወልቂጤ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።
እስካሁን አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት ካስተናገዱ አራት የሊጉ ክለቦች ተርታ የሚገኘው ወልቂጤ ከድል ማግስት ሌላኛውን ከአሸናፊነት ከመጣ ክለብ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ሲጠበቅ ቡድኑም ጨዋታውን አሸንፎ ከሊጉ መሪ ፋሲል ጋር ነጥቡን ለማስተካከል እያለመ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል።
በሰባተኛ ሳምንት የሊጉ የመክፈቻ መርሐ-ግብር አዲስ አበባ ከተማን ያሸነፈው ወልቂጤ በዕለቱ ሦስት ነጥብ ከማግኘቱ በተጨማሪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም መልካም የሚባል ነበር። በተለይ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲጥር የነበረበት መንገድ ተጋጣሚው አደጋዎችን እንዳይፈጥርበት ያደረገ እና መከላከሉን ከኳስ ጋር እንዲቃኝ ያደረገ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የኳስ ቁጥጥሩ ፍጥነትን ጨምሮ የነበረ መሆኑ ለአዲስ አበባዎች ፈተና የሆነ ነበር። ከዚህ ውጪ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ተስፋዬ ነጋሽ እና ረመዳን የሱፍ እጅግ ወደ ፊት እየሄዱ እንዲጫወቱ እና የተጋጣሚ ተከላካዮች እንዲዘረዘሩ ሲያደርግ ነበር። ይህ አጨዋወት በነገው ጨዋታ ቀዝቀዝ ብሎ እንደሚመጣ ሲጠበቅ ነገርግን ቡና ካለበት የሽግግር ችግር አንፃር የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቶች ሊደጋገሙ ይችላሉ።
ከላይ እንደጠቀስነው የመስመር ተከላካዮቹ በማጥቃት ሲሶ ላይ እንዲገኙ ፍቃድ ቢሰጣቸውም የመጨረሻ ኳሶቻቸው ግን ፍሬያማ ሲሆኑ አይታይም ነበር። በተለይ በቀኝ መስመር ቦታ ተሰልፎ የነበረው ተስፋዬ በተደጋጋሚ ጥሩ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚችልበት ቦታ እየተገኘ በውሳኔ ችግሮቹ ያመከናቸው ኳሶች ነበሩ። እሱ ብቻ ሳይሆን የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችም ይህ ክፍተት ይስተዋልባቸዋል። የነገ ተጋጣሚያቸው ቡና ኳስ ነፍጓቸው ሊጫወት ስለሚችል ግን ጨዋታውን ማሸነፍ ከፈለጉ ሊያገኟቸው የሚችሉትን ዕድሎች በራሳቸው ችግር ማምከን አይገባቸውም። ከላይ እንደጠቀስነው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እና ቀጥተኛ እንቅስቃሴ ቡና ኳስ ለመመስረት የሚጥርበትን መንገድ ከማጨናገፍ ስልት ጋር ተዳምረው በወልቂጤ በኩል ልናየው የምንችለው አጨዋወት ይሆናል።
እስከ አምስተኛ ሳምንት ድረስ አንድም ጨዋታ ሳያሸንፍ የተጓዘው ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ያሸነፋቸውን ጨዋታዎች ቁጥር ወደ አራት ለማሳደግ እና ከሊጉ መሪዎች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ በጠንካራ መንገድ ራሱን አዘጋጅቶ ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይታመናል።
ኢትዮጵያ ቡና በማይቀየረው መርሆው እንደሁል ጊዜው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ይዞ እንደሚጫወት ይጠበቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ የመዋቅሩ ዋና ክፍል የሆነው የአማካይ መስመሩ በሮቤል እና ዊሊያም ሲመራ የቆየ ሲሆን የታፈሰ ሰለሞን ወደ ሜዳ መመለስም ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆነው ይታመናል። ባለፉት ጨዋታዎች ተከላካዮችን የመረበሽ ብቃቱ ጎልቶ እየታየ የሚገኘው ዊሊያም በድሬዳዋው ጨዋታ ለተገኙት ፍፁም ቅጣት ምቶችም መነሻ የነበረ መሆኑ ነገም በወልቂጤ የተከላካይ እና የአማካይ ክፍል መሀል ክፍተቶችን የማነፍነፍ ብቃቱ ለእነአቡበከር ናስር ትክክለኛው ቦታ ላይ መገኘት ልዩነት ሊፈጥር ተብሎ እንዲታሰብ ያደረጋል። መሰል ተጫዋቾች በራስ መተማመናቸው ከፍ ብሎ መገኘት በአንድ ለአንድ ግንኙነት ላይ አሸንፈው እንዲወጡ ለማድረግ ከማስቻሉ አንፃር ቡና ተጋጣሚው ወደ ኋላ ካፈገፈገ የዊሊያምን ግልጋሎት አብዝቶ ሊሻ ይችላል።
ለኢትዮጵያ ቡና የነገው ጨዋታ ከድሬዳዋው አንፃር ሊለያይ ይችላል። በድሬው ጨዋታ ተጋጣሚው በኳስ ቁጥጥር ላይ እምብዛም አላስቸገረውም ነበር። ወልቂጤ ግን ኳስ ቁጥጥርን ከመልሶ ማጥቃት ጋር እንደየሁኔታው እየቀያየረ ሲጫወት ማስተዋላችን ቡናዎች ኳስ ከመቆጣጠር ፍልሚያ ባለፈ የመከላከል ሽግግራቸው ጥሩ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባቸው እንረዳለን። በእርግጥ በድሬው ጨዋታ መሰል ሂደቶችን በአግባቡ ሲቆጣጠሩ ያየን ሲሆን እንደ ጌታነህ ከበደ ልምድ ያለው የወልቂጤ የፊት ክፍል በተለየም ሳጥኑ መግቢያ ላይ ኳሶችን ሲነጥቅ በፍጥነት የሚሞክርበትን መንገድ በአግባቡ ማምከን ከቡናማዎቹ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ቡናው አቤል ማሞ ቅጣቱን ከመጨረሱ ውጪ ሁለቱም ቡድኖች ያለጉዳት እና ቅጣት ዜና ጨዋታቸውን ይከውናሉ።
ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በመሀል ዳኝነት ትመራዋለች።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– አምና በሊጉ የመጀመሪያ ግንኙነታቸውን ሲያደርጉ በመጀመሪያው ዙር 2-2 ተለያየተው በቀጣዩ ኢትዮጵያ ቡና 2-1 ማሸነፍ ችሏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
ስልቪያን ግቦሆ
ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ውሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ
ሀብታሙ ሸዋለም
ያሬድ ታደሰ – በኃይሉ ተሻገር
አብዱልከሪም ወርቁ
ጌታነህ ከበደ – እስራኤል እሸቱ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
በረከት አማረ
ኃይሌ ገብረተንሳይ – ወንድሜነህ ደረጀ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሥዩም ተስፋዬ
ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊልያም ሰለሞን
ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ