ከደቂቃዎች በፊት የተጠናቀቀው የአርባምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ አርባምንጭን ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች መሪ ቢያደርግም በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
ከጅማ አባጅፋር ጋር ነጥብ ተጋርተው የመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ከመጀመሪያ አሰላለፋቸው አራት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ማርቲን ኦኮሮ፣ አሸናፊ ተገኝ፣ ሱራፌል ዳንኤል እና በላይ ገዛኸኝ አርፈው አንድነት አዳነ፣ መላኩ ኤሊያስ፣ ወርቅይታደስ አበበ እና ኤሪክ ካፓይቶ በመጀመሪያ አሰላለፍ ቦታ አግኝተዋል። አዳማ ከተማ በበኩሉ በተመሳሳይ ያለ ግብ ከተለያየበት የጊዮርጊስ ጨዋታ ሁለት የተጫዋች ለውጥ አድርጓል። በዚህም ዮናስ ገረመውን በኤሊያስ ማሞ እንዲሁም አቡበከር ወንድሙን በጅብሪል አህመድ ተክቶ ጨዋታውን ቀርቧል።
ጥሩ ፉክክር ማሳየት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና ከጅምሩ ቀልብን ይዞ የዘለቀ ነበር። በ9ኛው ደቂቃም የአዳማው የግብ ዘብ ጀማል ጣሰው ኳስ ለማፅዳት ሲሞክር ሙና በቀለ አግኝቶት በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት ቡድኑን መሪ ሊያደርግ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ራሱ ሙና ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኬኒያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ በሩቁ ቋሚ በመጠበቅ በግንባሩ ከመረብ ጋር አዋህዶት አዞዎቹ መሪ ሆነዋል። በግቡ መቆጠር ሂደት ኳሱን አመቻችቶ ያቀበለው ሙና ኳሱን ሲረከብ እንዲሁም ግቡን ያስቆጠረው ካፓይቶ ከሙና የተነሳውን ኳስ ለመጠቀም ሲጥር ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ እንደነበሩ ቢታይም የዕለቱ የመስመር ዳኛ ሳይመለከቱት ቀርተው ግቡ ፀድቋል።
በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የነበረውን ፈጣኑን የአርባምንጭ የማጥቃት እንቅስቃሴ መቆጣጠር ያልቻሉት አዳማዎች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ተደጋጋሚ የመከላከል ስህተቶችን እየሰሩ ነበር። በ15ኛው ደቂቃም ቶማስ ስምረቱ ጥፋት ሰርቶ ከጥሩ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ሀቢብ ለመጠቀም ሲጥር ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ይሁ ግዙፍ ተከላካይ ኳስ ለግብ ጠባቂው አቀብላለሁ ብሎ ያሳጠረውንም ኳስ ሀቢብ አግኝቶ ሁለተኛ ግብ ሊያደርገው ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመግባት የሞከሩት አዳማዎችም በ23ኛው ደቂቃ አስደንጋጭ ጥቃት ፈፅመው ተመልሰዋል። በዚህም አሜ መሐመድ በግራ መስመር የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ሳጥን አሻምቶት የነበረ ሲሆን የቡድን አጋሮቹ ኳሱን ከማግኘታቸው በፊት ግን የአርባምንጭ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል።
በ36ኛው ደቂቃም አዳማዎች አቻ ለመሆኑ የጣሩበት የግብ ማግባት አጋጣሚ ታይቷል። በተጠቀሰው ደቂቃ የተገኘውን የቅጣት ምት ኤሊያስ ማሞ አሻምቶት ፀጋዬ አበራ በግንባሩ ሲመልሰው ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ የነበረው አሜ አግኝቶት ግብ ሊያደርገው ነበር። ነገርግን አሜ የመታውን ኳስ ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታዎች ተመራጭ የሆነው ግብ ጠባቂ ይስሀቅ ተገኝ ተቆጣጥሮታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሌላ እጅግ ለግብ የቀረቡበትን ሁነት የአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ተጫዋቾች ፈጥረዋል። በዚህም ኤሊያስ እና አብዲሳ በጥሩ መናበብ የተቀባበሉትን የመጨረሻ ኳስ ኤሊያስ ወደ ግብ ሲመታው ይስሀቅ ይመልሰዋል። የተመለሰውን ኳስ ደግሞ እዛው ሳጥን ውስጥ የነበረው አሜ አግኝቶት ለአብዲሳ ቢያመቻችለትም አብዲሳ በወረደ አጨራረስ አጋጣሚውን በአስቆጪ ሁኔታ አምክኖታል። አጋማሹም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ አርባምንጭን መሪ አድርጎ ተጠናቋል።
የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት አዳማዎች ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ በተደጋጋሚ የአርባምንጭን የግብ ክልል ለመጎብኘት ሲጥሩ ነበር። በ53ኛው ደቂቃ ግን ሀቢብ ቶማስ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ራሱ በመምታት ተነሳሽነታቸው ላይ ውሃ ሊከልስ ነበር። በግራ እግር የተመታውን የሀቢብ ኳስ ግን ጀማል አውጥቶታል። ከሁለቱ የአዳማ የአጋማሽ ለውጦች አንዱ የሆነው አቡበከር ወንድሙ ደግሞ በ56ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረን ኳስ በግንባሩ ሲሞክር የግቡ ቋሚ እና ይስሀቅ ተባብረው አምክነውበታል።
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ ወስደው መጫወት የቀጠሉት አዳማዎች የአርባምንጭ ተጫዋቾችን ማፈግፈግ ተከትሎ የተሻለ የጨዋታ ብልጫ ኖሯቸዋል። ወደ አቻነት ለመምጣትም ጥረቶችን አጠናክረው ይዘዋል። በ66ኛው ደቂቃ ዳዋ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ እንዲሁም በ68ኛው ደቂቃ አማኑኤል ጎበና ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ለመጠቀም ጥሮ ነበር። በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት የተንቀሳቀሱት አርባምንጭ ከተማዎች በ76ኛው ደቂቃ ቀይረው ያስገቡት አቡበከር ሻሚል ከተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ እና ኳሱን ለማፅዳት የወጣውን ጀማል አልፎ ወደ ግራ ካዘነበለ ቦታ ያገኘውን የመጨረሻ ኳስ ወደ ግብ መትቶ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ኳሱ ዒላማውን ስቶበት ቀርቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ የግቡ ባለቤት ካፓይቶ ሁለተኛ ግብ ለማግኘት ተቃርቦ ጀማል በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ ሦስት ደቂቃ ሲጨመር ግን አዳማ አቻ የሆነበትን ጎል ከዳዋ አግኝቷል። በዚህም ከቅጣት ምት የተነሳውን ኳስ ግብ ጠባቂው በሚገባ ማፅዳት ተስኖት ዳዋ አግኝቶት መረብ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በውጤቱ መሠረት አራተኛ ተከታታይ አቻ ያስመዘገቡት አርባምንጮች ነጥባቸውን አስራ አንድ አድርገው ወደ ስምንተኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ አምስተኛ ተከታታይ የአቻ ውጤት ያገኙት አዳማዎች ደግሞ ነጥባቸውን ዘጠኝ አድርሰው ወደ አስራ አንደኛ ደረጃ አድገዋል።