የዋልያዎቹ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ ሞሮኮ ከማምራታቸው በፊት መግለጫ ሰጥተዋል።
መጋቢት 15 እና 18 ከጊኒ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ሁለቱን ፍልሚያዎች ወደሚያደርግበት ሞሮኮ ጉዞውን ያደርጋል። ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ስፍራው ከማቅናቱ በፊት አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዲሁም የሜዳ ላይ ጉዳዮችን በተመለከተ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ መግለጫ የሰጡ ሲሆን አስተዳደራዊ ሀሳቦችን ከደቂቃዎች በፊት አስነብበን ነበር። አሁን ደግሞ የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ የዝግጅት ጊዜያትን በተመለከተ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበናል።
\”ለጊኒው የደርሶ መልስ ጨዋታ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገን ከመጋቢት 6 ጀምሮ ዝግጅታችንን ማድረግ ጀምረናል። ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ብናደርግም በህመም እና በክለብ ግዴታ ምክንያት ያልተገኙ ተጫዋቾች አልተቀላቀሉንም። አቡበከር ናስር በጉዳት ይገዙ ቦጋለ አንድ ቀን አብሮን ልምምድ ሰርቶ የጉልበት ሊጋመንት ጉዳት ማስተናገዱ በኤም አር አይ በመታወቁ ከስብስባችን ውጪ ሆኗል። በእነሱ ምትክ ለቡድኑ አዲስ ያልሆኑ ተጫዋቾችን ተክተናል።
\”ከልምምድ ውጪ ከሩዋንዳ ጋር በትናትናው ዕለት የአቋም መፈተሻ አድርገናል። የ4 ቀን ልምምድ ተሞክሮ ከዚህ በፊት አልነበረንም። ቢሆንም ግን ትናንት ያደረግነው ጨዋታ ላይ ያየነው ነገር ጥሩ የሚባል ነው። በዝግጅቱም ሆነ በትናንቱ ጨዋታ ጥሩ ነገር አይተናል።\” ብለዋል።
በስብስቡ ውስጥ የሚገኙት ተጫዋቾች በጥሩ ተነሳሽነት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አሠልጣኝ ውበቱ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሀሳባቸው ዋናውን ውድድር መቀላቀል እንደሆነ ተናግረዋል። \”በዋናነት ፍላጎታችን የ2023ቱን የአፍሪካ ዋንጫ መቀላቀል ነው። ለዚህ ደግሞ የጊኒው የደርሶ መልስ ጨዋታ ወሳኝ ነው። በዚህም ከጨዋታዎቹ የበለጠውን ነጥብ ለማግኘት እንጥራለን። 6 ነጥብ መሪነታችንን ያስቀጥላል ፤ ቢያንስ ግን 4 ነጥብ ለማሳካት ነው ጨዋታዎቹን የምናደርገው\” የሚል ሀሳባቸውን በስፍራው ለሚገኙ የብዙሀን መገናኛ አባላት አጋርተዋል።
ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን የጨዋታ መንገድ ጋር በተገናኘ በተለይ ከቆሙ ኳሶች እና ተሻጋሪ ኳሶች ጋር ተያይዞ ቡድኑ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነና የተጋጣሚ ቡድን የተካነበትን የአጨዋወት መንገድ ማጥፋት ስለማይቻል በተቻለ መጠን ለመቀነስ እየተዘጋጁ እንደሆነ አመላክተዋል።
ከዚህ ውጪ በልምምድ ወቅት መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደው ረመዳን ጉዳቱ ለክፉ እንደማይሰጠው ጠቁመዋል።
አሠልጣኙ በንግግራቸው ማብቂያ የልምምድ ሜዳ የተባበሩዋቸውን ኢቲቪ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን አመስግነዋል።