በዛሬው የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ሰበታ ከተማን 3-2 በማሸነፍ ደረጃውን ያሻሻለበትን ውጤት አስመዝግቧል።
ሰበታ ከተማ የመጀመሪያ ድል ካሳካበት የጅማው ጨዋታ ፍፁም ተፈሪን በሀምዛ አብዱልመን ተክቶ ጨዋታውን ጀምሯል። በወልቂጤ በኩል በተደረጉ ስድስት ለውጦች ቅጣት ያገኘው ሲልቪያን ግቦሆ በ ሰዒድ ሀብታሙ ፣ ተከላካዮቹ ውሀብ አዳምስ እና ተስፋዬ ነጋሽ በዳግም ንጉሴ እና ዮናታን ፍስሀ ፣ አማካዮቹ በኃይሉ ተሻገር እና ያሬድ ታደሰ በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ጫላ ተሺታ እንዲሀም አጥቂው እስራኤል እሸቱ በአህመድ ሁሴን ተተክተዋል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የወልቂጤ ከተማ ክለብ ፕሬዘዳንት አቶ እንዳለ ገብረመስቀል ለዋሊያዎቹ አምበል ጌታነህ ከበደ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማበርከት ለብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ከጅምሩ ወደ ፊት ገፍቶ የመጫወት ምልክት የታየበት አጋማሽ የቅጣት ምት ዕድሎችን በፈጠሩላቸው እንቅስቃሴዎች ጀምሮ ብዙም ሳይቆይ ግብ አስተናግዷል። 9ኛው ደቂቃ ላይ ሰዒድ ሀብታሙ በረጅሙ ያራቀው ኳስ በሰበታ ተከላካዮች አንተነህ ተስፋዬ እና ኃይለሚካኤል አደፍርስ ተጨርፎ የደረሰው አህመድ ሁሴን ወልቂጤን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።
ምላሽ ለመስጠት ፈጠን ባለ ጥቃት ወደ ወልቂጤ አጋማሽ አመዝነው መጫወት የጀመሩት ሰበታዎች 14ኛው ደቂቃ ላይ በሳሙኤል ሳሊሶ ቅጣት ምት ለግብ ቢቃረቡም አግዳሚው መልሶባቸዋል። ሳሙኤል ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከቀኝ መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን የላካትን ኳስ የወልቂጤ ተከላካዮችን ስታልፍ ፍፁም ገብረማሪያም በቀላሉ ጎል አድርጓታል። ከግቡ በኋላም ሰበታዎች የተሻለ ኳስ በመያዝ በቅብብል ወደ ሳጥን ለመድረስ ሲጥሩ ታይተዋል። ሆኖም ወልቂጤዎች ከመሀል የሚጥሏቸው ኳሶች ከሰበታ የተከላካይ መስመር ጀርባ እያረፉ እና የለዓለም ብርሀኑ ጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮባቸው አደገኛ ቅፅበቶችን ሲፈጥሩ ይታይ ነበር።
ከውሀ ዕረፍቱ በኋላም ሰበታ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። በአመዛኙ ወደ ቀኝ ባደላ ጥቃታቸው ወደ ሳጥን ውስጥ ይልካቸው ከነበሩ ኳሶችም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ነበር። በተለይም 37ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከዚሁ አቅጣጫ ያደረሰውን ኳስ ፍፁም ወደ ግብ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ላይ ተነስቶበታል። ረዘም ባሉ ኳሶች ወደ ሳጥን መድረስን ምርጫቸው ያደረጉት ወልቂጤዎች ግን ከዕረፍት በፊት ግብ አግኝተዋል። አንተነህ ተስፋዬ በጫላ ተሺታ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ 45ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አገናኝቶ ወልቂጤን ዳግም መሪ አድርጓል።
ሁለተኛው አጋማሽ በቡድኖቹ የተፈራረቀ ማጥቃት ሲቀጥል የሁለቱን ግብ ጠባቂዎች አቅም የፈተኑ ረዘም ያሉ ኳሶች ከቅጣት ምት እና ከጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ሳጥን ሲጣሉ ይታይ ነበር። 58ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች የሰበታዎችን ደካማ የመከላከል አደረጃጀት በቀኝ መስመር በኩል አልፈው በገቡበት አጋጣሚ ግን አህመድ ሁሴን ከሀብታሙ ሸዋለም የደረሰውን ኳስ አክርሮ በመምታት የወልቂጤን መሪነት ያሰፋች ግብ አስቆጥሯል። ቀጣዩ የጨዋታው ዓይን ሳቢ ቅፅበት 63ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ የቢያድግልኝ ኤልያስ ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ በጌታነህ ከበደ እጅ ቢመለስም ከአርቢትሩ እይታ ውጪ ሆኖ አልፏል።
ሰበታዎች ቀጣዩን አደገኛ ሙከራ ሲያደርጉ 69ኛው ደቂቃ ላይ ኃይለሚካኤል አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ በተከላካዮች መሀል የሰነጠቀውን ኳስ ከግራ ወደ ሳጥን ሲያደርስ ዱሬሳ ነፃ ሆኖ ያደረገው አደገኛ ሙከራ ወደ ላይ ተነስቷል። ሰበታዎች ቅያሪዎችን በማድረግ ግብ ፍለጋ ወደ ፊት ገፍተው መንቀሳቀስ ሲቀጥሉ ወልቂጤዊች የመልሶ ማጥቃት ባህሪን ተላብሰው ይታዩ ነበር። በዚህ ሁኔታ በቀጠለው ጨዋታ ሳሙኤል ሳሊሶ 84ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት በጠንካራ ምት የቅጣት ምት ጎል አስቆጥሮ ሰበታን ወደ ጨዋታው መልሷል። እስከ ጨዋታው ፍፃሜም ሰበታዎች ተጭነው በመጫወት የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ቢጥሩም የተከላካይ ቁጥራቸውን የጨመሩት ወልቂጤዎች ይህ እንዳይሆን በማድረግ ጨዋታውን ጨርሰዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማዎች ነጥባቸውን 15 አድርሰው ቀሪ ጨዋታዎች እስኪደረጉ ከስድስት ወደ ሁለተኛነት ከፍ ብለዋል።