የዕለቱ የመጀመሪያው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ሁለቱ አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ
ስለጨዋታው
“ከመሪዎቹ ላለመራቅ ነጥቡ ያስፈልገን ነበር ይህንንም አሳክተናል ፤ 25 ተጫዋቾችን እስከያዝክ በጉዳት በምናምን ማሳበብ አያስፈልግም የዛሬውም ጨዋታ ይህን ያየንበት ነበር።”
በመጨረሻ ደቂቃ ጫና ውስጥ ስለመግባታቸው
“አፈግፍገን መጫወት አልነበረብንም እዚህ ሜዳ ላይ አንድ ጎል ያስቆጠረ ቡድን አሸንፎ ሲወጣ እየተመለከተን ነበር የእኛ ጨዋታ ግቦችም በብዛት ማስቆጠራችን አጥቅተን ስለመጫወታችን ያሳያል ያው ግን ተጫዋቾች ውጤቱን ለማስጠበቅ ከመጓጓት በተወሰነ መልኩ አፈግፍገን ነበር ይህም ሰበታ ጫና እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል።”
ስለ ዘጠኝ ሳምንቱ ጉዟቸው
“ክለቡ እና እኔ የተነጋገርነውን እናውቃለን ነገርግን እኔ ዘንድሮ ለዋንጫ መጫወት እፈልጋለሁ ምክንያቱም ያሉኝ ልጆች ይህን ለማድረግ የሚችሉ ስለሆነ ይህን ለማደረግ በክለቡ ዙርያ ያሉ ሁሉ ሊያግዙን ይገባል ፤
ያለውን ውጤት አስጠብቆ ለመሄድ ሁሉን ነገር ማድረግ ያስፈልጋል በውጤቱ ሁሉም ደስተኛ ነው በእረፍት ጊዜያችን ሁሉም ነገር
ይደረጋል ብዬ እጠብቃለሁ።”
ስለአፍሪካ ዋንጫው
“በተጫዋችነት ዘመኔ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ባለመቻሌ በጣም ያናድደኛል አሁን ግን በማሰለጥናቸው ልጆች ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን የተለየ ስሜት አለው። አይደለም ሰንደቅ አላማ መረከብ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት በራሱ ያለውን ስሜት እናውቀዋለን ስለዚህ ይህን ትልቅ ሀላፊነት ተወጥተውት ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ።”
ስለ የፀጉር ቁርጡ
“ይሄ በተጫዋችነት እቆረጠው የነበረው የፀጉር ቁርጥ ነው ፤ ፀጉር የለውም መላጣ ነው ሲሉ ለነበሩት ምላሽ ነው።”
ዘላለም ሽፈራው – ሰበታ ከተማ
በጨዋታቸው ስለገጠማቸው ነገር
“የመከላከል አደረጃጀታችን ፍፁም ደካማ ነበር ለዚህም የተቆጠሩብን ግቦች ማሳያ ናቸው።”
ከእረፍት በኃላ ስለተደረጉት ቅያሬዎች
“አንድም 3-1ተመርናል ከዚህ በኃላ አጥቅቶ ከመጫወት ውጭ አማራጭ አልነበረንም ለዚህም የአብዱልሀፊዝ እና የበሀይሉ ቅያሬ ወደ ፊት አጥቅተን የመጫወት አቅማችንን አሳድጎልናል በዚህም እድሎችን መፍጠር ችለናል ስለዚህ ጥሩ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።”
ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ስላላቸው ተስፋ
“ሁለት ነገሮች ናቸው አንደኛው ከውድድሩ አጋማሽ በፊት ዝውውር መፈፀም አይቻልም ስለዚህ ባለን ነገር ጠጋግነን የተሻለ ነገር ለመፍጠር መስራት ይኖርብናል ሁለተኛው ክፍተቶች አሉብን በምንላቸው ቦታዎች ላይ ተጫዋቾችን ማዘጋጀት ይኖርብናል።”
ስለአፍሪካ ዋንጫው
“ከስምንት አመታት በኃላ ዳግም መመለሳችን ለማንኛውም ዜጋ ደስታ የሚሰጥ ነው ፤ ከደሰታም ባለፈው ባለሙያውም ሆነ ሌላው በሚችለው አቅም ቡድኑን ማገዝ ይኖርብናል። በውድድሩ ተሳትፎ መመለስ በራሱ ግብ ሊሆን አይችልም የተሻለ ጉዞን በማድረግ ለሀገር እንዲሁም ለባለ ድርሻ አካላት ውጤት እንዲያስገኙ እንመኝላቸዋለን።”