ሊጉ በቀጣይ ቀናት በአዳማ ከተማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ከተቋረጠበት የሚቀጥል ይሆናል።
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ17ኛ ሳምንት በድሬደዋ ስታዲየም የመጀመሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከኢትዮጵያ ቡና አገናኝቶ ጨዋታው ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ በከተማው ያለማቋረጥ በተከታታይ ቀናት በጣለው ከባድ ዝናብ ቀሪ የ17ኛ ሳምንት ሰባት ጨዋታዎች መሰረዛቸው ይታወቃል።
አወዳዳሪው አካል በቀጣይ በተመረጠው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች መልስ ከ18ኛው ሳምንት በኋላ ባለው ወቅት በተስተካካይ መርሃ ግብር የሚካሄዱ መሆኑን ከዚህ ቀደም መግለፁ ይታወሳል።
ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ነገ ወደ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚመለስ መሆኑን ተከትሎ ከፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 23 ጀምሮ ውድድሩ የሚጀመር መሆኑ ሲታወቅ ቀጥታ ከ18ኛው ሳምንት ከመጀመር ይልቅ በ17ኛው ሳምንት ያልተካሄዱ ሰባት ተስተካካይ ጨዋታዎችን በማካሄድ መጀመር መታሰቡን ሰምተናል።
በተስተካካይ ጨዋታዎች ውድድሩ ይጀምር እንጂ አጠቃላይ በአዳማ የሚኖሩ ውድድሮች ፕሮግራም ነገ አልያም ከነገ በስቲያ አወዳዳሪው አካል ይፋ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።
በ17ኛ ሳምንት ያልተካሄዱ ጨዋታዎች
ሲዳማ ቡና ከ ሀድያ ሆሳዕና
መቻል ከ አዳማ ከተማ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ድሬደዋ ከተማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ
ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ
ኢትዮጵያ መድን ከ አርባምንጭ ከተማ
ወልቂጤ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ