አወዛጋቢ የነበረችው የከነዓን ማርክነህ ግብ ፈረሰኞቹን ከመሪው ፋሲል ከነማ በአንድ ነጥብ ብቻ አንሰው በሊጉ በሁለተኝነት እንዲቀመጡ አድርጋለች።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻው ድል ባደረገው ብቸኛ ለውጥ ቸርነት ጉግሳ በአማኑኤል ገብረሚካኤል ቦታ ጨዋታውን ጀምሯል። ጅማ አባ ጅፋሮች ደግሞ ከሰበታው ሽንፈት በላይ አባይነህ ፣ ሚኪያስ ግርማ እና ዳዊት ፍቃዱን በተስፋዬ መላኩ ፣ ሽመልስ ተገኝ እና ከሰባት ጨዋታ ቅጣት በተመለሰው በዳዊት እስጢፋኖስ ተክተዋል።
በጨዋታው ጅማሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ የእንቅስቃሴ የበላይነቱን ወስዷል። የቡድኑ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ተጋጣሚው ወደ ራሱ ሜዳ እንዲያፈገፍግ ያስገደደም ነበር። በእርግጥ የጊዮርጊስ ቅብብሎች የጅማን የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ ለመግባት ቀላል አልሆነላቸውም። ቡድኑ በጅማ ሳጥን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አደጋ የጣለው 12ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ከቀኝ በከፈቱት ጥቃት ሱለይማን ሀሚድ ከአቤል ያለው ተቀብሎ መሬት ለመሬት ወደ ግብ የላከውን ኳስ ሁለተኛው ቋሚ ላይ ኢስማኤል ኦውሮ አጎሮ ተንሸራቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ለጥቂት ሳይሳካለት ቀርቷል። ቀስ በቀስ ከኳስ ጋር ከሜዳቸው መውጣት የጀመሩት ጅማዎችም በበኩላቸው በቶሎ ወደ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ቢታዩም ስኬታማ ጥቃት መሰንዘር ግን አልቻሉም።
ከወሀ ዕረፍቱ መልስ ጅማ አባ ጅፋሮች የተጋጣሚያቸው ጫና ወደ ግብ ክልላቸው እንዳይቀርብ በማድረግ ገፍተው ተጫውተዋል። በዚህም የጊዮርጊሶች በቅብብል ላይ የተመሰረቱ አስፈሪ የማጥቃት ሂደቶች እየከሰሙ በረጃጅም ኳሶች እየተተኩ ሄደዋል። በዚህ ይሳካላቸው እንጂ የጅማዎችም አልፎ አልፎ የሚታይ የመልሶ ማጥቃት ሂደት ባልተሳኩ የመጨረሻ ቅብብሎች እየከሸፈ ጨዋታው ከቡድኖቹ የማጥቃት ሂደት የመነጨ ከባድ ሙከራ ሳይታይበት ወደ ዕረፍት እንዲያመራ ሆኗል።
ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ቀኝ ያደለ ጥቃት ያመዘነበት ነበር። ሆኖም የመጀመሪያው ሙከራ የታየው 55ኛው ደቂቃ ላይ የአቤል ያለውን የማዕዘን ምት ጋቶች ፓኖም በግንባር ገጭቶ በግቡ አግዳሚ ሲመለስበት ነበር። ቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጨዋታው ግለት በድንገት ከፍ ብሎ ወደ ሁለቱም ሳጥኖች ያመሩ ፈጣን የማጥቃት ሂደቶችን አሳይቶናል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የነበረው 3ለ4 በሆነ የቁጥር ብልጫ 59ኛው ደቂቃ የጅማዎች የሰነዘሩት መልሶ ማጥቃት ሲሆን መሀመድኑር ናስር ከእዮብ ዓለማየሁ ተሰብሎ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ በጨዋታ ውጪ ውሳኔ ሳይፀድቅለት ቀርቷል።
ለአፍታ የታየው ግለቱ ወደ ቀደመው መንፈሱ የተመለሰው ጨዋታው አልፎ አልፎ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ፊት ከሚጣሉ ኳሶች የሚደረጉ ጥረቶችን እያሳየን ቀጥሏል። የተሻለ ሊባል በሚችል ሙከራ ተቀይሮ የገባው ዳዊት ፍቃዱ 77ኛው ደቂቃ ላይ ከጊዮርጊስ ተጫዋቾች ያስጣለውን ኳስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የስታዲየሙ መብራቶች በከፊል ጠፍተው ጨዋታው ተቋርጧል።
ጨዋታው ከ13 ደቂቃዎች መቋረጥ በኋላ ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ81ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም በአጭር የጀመሩትን ኳስ ሀይደር ሸረፋ በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ከነዓን ማርክነህ በግንባሩ በመግጨት ፈረሰኞቹን መሪ ያደረገችን ግብ አስቆጥሯል። ተጨዋቹ በጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረ ቢሆንም ከዳኞች እይታ ውጪ ሆኖ ጎሉ ፀድቋል።
በተቀሩት ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን መሪነት በጥሩ መልኩ ለማስጠበቅ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋሮች ግን ጨዋታውን ውጤት ለመቀልበስ ያደረጉት ጥረት ውጤታማ መሆን ሳይችል ጨዋታው በፈረሰኞቹ የበላይነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን ወደ 17 ከፍ በማድረግ ከፋሲል ከነማ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ አድርጓል።