የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ረፋድ ላይ ሲጀመሩ ቦሌ ክፍለከተማ ጌዲኦ ዲላን 2ለ1 አሸንፏል። መከላከያ እና አዳማ ከተማ ደግሞ ያለ ጎል አጠናቀዋል፡፡
3፡00 ሲል ጌዲኦ ዲላ እና ቦሌ ክፍለከተማ ተገናኝተው የቦሌን ክፍለከተማ አስደናቂ ብቃት አይተንበት ተጠናቋል፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በተለይ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች የአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻው ቦሌ ኳስን በሚገባ በመቆጣጠር ለአጥቂዋ ንግሥት በቀለ ተሻጋሪ ኳሶችን በመላክ ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ቀስ በቀስ ደቂቃዎች እየገፋ ሲመጣ ጌዲኦ ዲላ ወደ ጨዋታ ሪትም ሲገባ የተመለከትን ቢሆንም የወጥነት ችግር ጎልቶ ይንፀባረቅባቸው ነበር፡፡
18ኛው ደቂቃ ላይ የጌዲኦ ዲላዋ አጥቂ ቤተል ጢባ ከርቀት ወደ ግብ ሞክራ ሁለት ደቂቃዎች መቆጠር እንደቻሉ ማለትም 20ኛው ደቂቃ ላይ አምበሏ አዲስ ንጉሤ መሀል ለመሀል አሾልካ የሰጠቻትን ቤተል ጢባ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ወደ ጎል በመምታት አስቆጥራ ጌዲኦ ዲላን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡
በኳሱ ቁጥጥሩ ሻል ቢሉም አብዛኛዎቹ የልምድ ችግር ያለባቸው የሚመስሉት ቦሌዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ንጋት ጌታቸው በሳጥን ውስጥ በቤተል ላይ በሰራችው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አዲስ ንጉሤ መታው የግቡ ቋሚ ብረት መልሶባታል፡፡ የጌዲኦ ዲላን በሂደት መዳከም ለመጠቀም በተሻጋሪ ኳሶች ላይ ትኩረት ያደረጉት ቦሌዎች 37ኛው ደቂቃ ሜላት አልሙዝ በቀጥታ ስትመታው የጌዲኦ ዲላዋ ግብ ጠባቂ መኪያ ከድርን ስህተት ተጠቅማ ንግሥት በቀለ ክለቧን 1ለ1 አድርጋለች፡፡
ጨዋታው ከመልበሻ ክፍል ሲመለስ ቦሌ ክፍለከተማዎች የተሻሻለ የሜዳ ላይ አቅማቸውን በሚገባ ሲያሳዩን የዋሉ ሲሆን በአንፃሩ ጌዲኦ ዲላዎች ወጣ ገባ ከሚል እንቅስቃሴ ውጪ በኳስ ቁጥጥሩ ሊበለጡ ግድ ሆኗል፡፡ አዲስ ንጉሤ ከቅጣት ምት ሞክራ ማህሌት ሺፈራው ከመለሰችባት ውጪ የጎላ ተፅእኖ ማድረግ የተሳናቸው ሲሆን በተቃራኒው የቦሌ ክፍለከተማዎች ተነሳሽነት ከፍ ያለበት ነበር፡፡ ንግሥት በቀለ ላይ ትኩረት ባደረገ የአጨዋወት መንገድ የቀጠሉት የመዲናይቱ ተወካይ የሆነው ቦሌ አንድ ለአንድ ንግስት በቀለ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ በሚያስቆጭ መልኩ ካመከነችው ኳስ በኋላ 81ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘችውን ኳስ ከመረብ አሳርፋዋለች፡፡
ስንታየው ኢርኮ ከግራ የጌዲኦ ዲላ ግብ ክልል በረጅሙ የሰጠቻትን ንግስት በቀለ በውድድሩ አራተኛ በጨዋታው ሁለተኛ ጎል አስቆጥራ ቡድኗን ከተመሪነት ወደ መሪነት አሸጋግራለች፡፡ በተደጋጋሚ በንግሥት ተጨማሪ አጋጣሚን ለማግኘት ቦሌዎች ጥረት ቢያደርጉም ጎል ሳይቆጠር በስተመጨረሻ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቤቲካ የጨዋታ ምርጥ በመባል ሁለት ጎሎችን ለቦሌ ያስቆጠረችሁ ንግስት በቀለ ተመርጣለች፡፡
ሁለተኛ በሆነው የመከላከያ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ አንድም ጎል ሳያስመለክተን ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡ ከጅምሩ ተመጣጣኝ የሚመስል የሜዳ ላይ ፉክክርን በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ መታዘብ የቻልን ቢሆን ከጠንካራ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ውጪ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመመልከት አልታደልንም። መከላከያ ከፊት ባሳለፏቸው አጥቂዎቹ ማለትም መሳይ ተመስገን ፣ ሴናፍ ዋቁማ እና ረሂማ ዘርጋው አማካኝነት ተደጋጋሚ የማግባት ቀዳዳዎችን ለማስከፈት ቢጥሩም ጥብቅ የነበረው የአዳማ ከተማ የተከላካይ ክፍልን አልፈው ግብ ማግኘት ግን አልቻሉም በተለይ ናርዶስ ጌትነት እና መሰሉ አበራ ለአዳማ የተከላካይ ክፍል የሰጡት ጥንካሬ ለዚህ ማሳያ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
20ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁና ከመሳይ ተመስገን የግራ መስመር ያገኘችሁን ኳስ በቀላሉ ማስቆጠር የምችል የነበረ ቢሆን በአዳማ ተከላካዮች ርብርብ ሊከሽፍባት ችሏል፡፡በአዳማ ከተማዎች በኩል ደግሞ ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ኳስን በመቆጣጠሩ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲያመሩ ማየት ብንችልም ፍፁም ይታይባቸው የነበረው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ግብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡በተለይ ሰርካዲስ ጉታ እና ምርቃት ፈለቀ ያገኙትን ዕድል አለመጠቀማቸው አዳማ በጊዜ መምራት እንዳይችል ያደረጉ ሁነቶች ነበሩ፡፡
ከእረፍት ሁለቱ ቡድኖች ሲመለሱ አዳማ ከተማዎች ከመከላከያ የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥሮ መታየት የቻለ ቡድን ሆኗል፡፡ በተለይ መሰሉ አበራ በተደጋጋሚ የተገኙ የቅጣት ምት ዕድሎችን ወደ ጎል የምትሎክበት መንገድ ግሩም ነበር። ከቅጣት ሞክራ በግቡ ቋሚ ለጥቂት የወጣባት እና 62ኛው ደቂቃ አሁንም ከቅጣት ምት መሰሉ መትታ ሂሩት ደሴ ስትመልሰው በድጋሚ ሰርካዲስ ጉታ አግኝታው በድጋሚ ሂሩት አድናባታለች፡፡መከላከያዎች በሙከራ ረገድ ተቀዛቅዘው በታዩበት በዚህኛው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃዎች እንደቀሩ የአዳማዋ ሰርካዲስ ጉታ ያለቀለትን አጋጣሚ አግኝታ በቀላሉ አምክናው ጨዋታው ያለ ጎል ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቤቲካ የጨዋታ ምርጥ በመባል የመከላከያዋ ገነት ሀይሉ ተመርጣለች፡፡