​ዋልያዎቹ በነገው ጨዋታ ወሳኝ ተጫዋቻቸውን ሊያጡ?

ነገ ከኬፕ ቨርድ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋቹን በጨዋታው ማግኘቱ አጠራጣሪ ሆኗል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ተወዳጁ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ይታወቃል። ከሁለት ሳምንት በፊትም ብሔራዊ ቡድኑ ቀድሞ ካሜሩን በመግባት ዝግጅቱን በጥሩ ሁኔታ ሲያከናውን የነበረ ሲሆን ነገ ምሽት 4 ሰዓትም የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን ከኬፕ ቨርድ አቻው ጋር ያደርጋል።

ትናንት በተደረገ የኮቪድ-19 ምርመራ ወደ ስፍራው ያቀናው 46ቱ ልዑክ ነፃ መሆኑ ሲገለፅ በግብፁ ክለብ አል ጎውና የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ግን ያለፉትን ቀናት መደበኛ ልምምድ እየሰራ እንዳልሆነ ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። በልምምድ ላይ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠመው ሽመልስ ትናንት እና ከትናንት በስትያ በተደረጉት ልምምዶች ላይ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን እንዳልሰራ ሲታወቅ ለብቻው ግን ከአካል ብቃት አሠልጣኙ ዶክተር ዘሩ በቀለ ጋር ቀላል ሥራዎችን ሲከውን ነበር። ለብቻው በሚሰራው ልምምድም ከዕለት ዕለት መሻሻልን እያሳየ እንደሆነ ተረድተናል።


ተጫዋቹ ለነገው ጨዋታ ብቁ ነው የሚለው ጉዳይም አሁን ያልተረጋገጠ ሲሆን ምሽት 3:30 በሚደረገው የቡድኑ የመጨረሻ ልምምድ ላይ በሚኖር ነገር እና የህክምና እንዲሁም የአካል ብቃት ባለሙያዎች በሚሰጡት ሀሳብ እንደሚወሰን ሰምተናል።