በቅርቡ የውስጥ ውድድሮቹን የሚጀምረው የአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን ከግዙፉ ሀገር በቀል ትጥቅ አምራች ተቋም ጋር ዛሬ የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ከሚገኙ ክለቦች እንዲሁም ከበርካታ የጤና እና የተለያዩ ቡድኖች ጋር የትጥቅ አቅርቦት ሥራዎችን በስፋት እየሰራ የሚገኘው ሀገር በቀሉ ተቋም ጎፈሬ ዛሬ ደግሞ የሥራ ደረጃውን ከፍ በማድረግ ከእግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት ፈፅሟል። በዚህም በኢትዮጵያ በሰሜም ምስራቅ ከሚገኘው የአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመስራት ዛሬ ቀትር ስምምነት ፈፅሟል።
በስምምነቱ ወቅት የአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽንን ወክለው ፕሬዝዳንቱ አቶ መሐመድ ያዩ አልዋን፣ ዋና ፀሐፊው አቶ ዓሊሚራ መሐመድ እና የሥራ አስፈፃሚ አባሉ አቶ ኢብራሂም ሙክታር ሲገኙ ጎፈሬን ወክለው ደግሞ መስራች እና ሥራ-አስኪያጁ አቶ ሳሙኤል መኮንን ተገኝተዋል። በቅድሚያም የአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስምምነቱን በተመለከተ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
“በስፖርት ትጥቅ በሀገራችን ከሚመረቱ እና በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚመረቱ ትጥቆች የማይተናነሱ እና ለዓይንም የሚማርኩ ማልያዎችን የሚያመርቱበትን ፋብሪካ ከጎበኘን በኋላ በእኛ ክልል ካለው ትልቅ የትጥቅ ችግር አንፃር የስፖርት ቤተሰቡ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ትጥቆችን ከጎፈሬ ምርቶች ተጠቃሚ መሆን የምንችልበት ሁኔታ መኖሩን ስናምን ከጎፈሬ ጋር ይህንን ስምምነት ለመፈራረም ወስነናል። መጀመሪያ ያገናኘን ከሌሎች የስፖርት አካላት ጋር ያደረጉት ስምምነት እና ለእነሱ የሰጡትን ድጋፍ ካየን በኋላ ድርጅቱ ለእኛም አስፈላጊ መሆኑን አምነን ጠቀሜታውን ስለተረዳን ነው። ትጥቆችን ከማግኘት አንፃር ብቻ ሳይሆን ሌሎች በማስታወቂያ ደረጃ ጉባዓዎችን በማዘጋጀት እና በማሳመር ሊረዱን እንደሚችሉ በማወቅ ከእነሱ ጋር ይህንን ስምምነት ልንፈራረም ችለናል።”
ፕሬዝዳንቱ አስከትለው ፌዴሬሽኑ ነው ወደ ጎፈሬ የመጣው ወይስ ጎፈሬ ነው ወደ ፌዴሬሽኑ የመጣው የሚለውን ሀሳብ በተከታዩ ንግግራቸው አንስተዋል።” እኛ ነን የመጣነው ፤ የሰሩትን ሥራ በማየታችን ነው የመጣነው። ስንመጣም እንደጠበቅነው እና ከዛም በላይ ሆነው ስላገኘናቸውም ጭምር ነው ስምምነት ላይ የደረስነው።”
አቶ መሐመድ በመጀመሪያ ገለፃቸው ማገባደጃ ላይም “ክለቦች በሚፈልጉት መልኩ ትጥቅ ከጎፈሬ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ እናመቻቻለን። በሌሎች ሊጎችም ውድድሮች በሚኖሩበት ጊዜ ትጥቆችን ለማግኘት እንችላለን ፤ የውድድር ፣ የልምምድ እና የመሳሰሉት። በእኛ ስር ያሉ ክለቦች የስምምነቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ስፖንሰርሺፕ በማፈላለግ እና ሌሎች ሁነቶችን በማዘጋጀትም ይረዱናል።” ብለዋል።
በመቀጠል መድረኩን የተረከበው የትጥቅ አምራች ተቋሙ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ የስምምነቱን ይዘት ማስረዳት ጀምሯል።
“ለሦስት ዓመት የሚቆይ ስምምነት ነው። ከትጥቅ አቅርቦቱ በተጨማሪ የገፅታ ግንባታ እና እግርኳሱን የማዘመን ከኢቨትንቶች ጋር በተያያዘ እና የማርኬቲንግ ሥራዎች እንዲሁም ክለቦቹ ራሳቸውን እንዲችሉ እንዴት ራሳቸውን በፋይናንስ እንደሚችሉ የማማከሩን ሥራ እንሰራለን። በአጠቃላይ ስምምነቱ የፓርትነርሺፕ ነው። እኛ ጋር ባለው ነገር የእነሱን እንሞላለን እኛ ጋር የሚጎለውን ነገር እነሱ እየሞሉ በጋራ ዘመናዊ እግርኳስ መገንባት ነው። በዚህ ውስጥ የእኛ ድርሻ ገፅታውን በማሳመር እና ሀሳቦችን በማቅረብ በጋራ ብዙ ርቀት ሄደን እንሰራለን ብለን እናስባለን። በፌዳሬሽን ደረጃ ስንሰራ ይህ የመጀመሪያው የፊርማ ሥነ ስርዓታችን ነው።
“በሀገራችን ያለው የትጥቅ ችግር ጎፈሬ ከመጣ ወዲህ በስፋት እየተቀረፈ ነው። አንዱም የጎፈሬ ድርሻ የስፖርት ትጥቅ ማቅረቡ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ውድድሮች ተጀምረው እስኪያልቁ ከትጥቅ ባሻገር ያሉትን ሂደቶች በጋራ አብረን እንሰራለን። አፋር ክልል ደግሞ እግርኳስ ላይ በሰፊው ኢንቨስት ማድረግ አስቧል። ከዚህ በፊት ተደርገው የማይታወቁ ትልልቅ ውድድሮችን የመጀመር ሀሳብ ስላለ በጋራ ትልቅ ሥራ እንሰራለን ብለን እናስባለን። ክልሉ በባህልም በግብዓትም ደረጃ እምቅ አቅም አለው ። ያንን ወደ እግርኳስ በማምጣት ብዙ ርቀት እንጓዛለን ብለን እናስባለን።”
ማብራሪያቸውን የቀጠሉት አቶ ሳሙኤል ስምምነቱን ለማድረግ የአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን የወሰነበትን ሂደት ጠቅሰዋል። “የአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን ይህንን ስምምነት ሲያደርግ ካሉባቸው ችግሮች መካከል አንዱ የትጥቅ ስለሆነ ነው። ከዛ አንፃር ከገበያ የሚገዛው ቁጥር የማፃፍ ፣ ራሳቸውን የሚገልፁ ማልያዎችን የመጠቀም ክፍተት ስላለበት ከክለቦቹ በመጣ ጥያቄ የተነሳ ነው። ስለዚህ ክለቦቹ ባናስገድዳቸውም ከእኛ ጋር እንደሚሰሩ እርግጥ ሆኗል። እናም የዛሬው የፊርማ ሥነ ስርዓት በጋራ የመስራት ሆኖ ዝርዝሩ በማማከር ፣ ትጥችን በማቅረብ እና ፕሮግራሞን በጋራ በማዘጋጀት ይሆናል ማለት ነው።”
በስምምነት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ዓሊሚራ መሐመድ እና የሥራ አስፈፃሚ አባሉ አቶ ኢብራሂም ሙክታርም የጎፈሬን ምርቶች ተዘዋውረው ሲያዩ በጥራቱ እንደተገረሙ ገልፀው በክልላቸው የሚገኙ ክለቦችም ይህንን በደስታ የሚቀበሉት እና በፍላጎታቸው የሚያደርጉት እንደሚሆን አመላክተዋል። በመጨረሻም ሁለቱ አካላት ስምምነታቸውን በወረቀት አስፍረው ዝግጅቱ ተጠናቋል።