በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር የበርካታ ወራት የተጫዋቾች ደሞዝ መክፈል ሲሳነው እስካሁንም ዝግጅት አልጀመረም።
የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ክለብ ጅማ አባጅፋር ዓምና ከሊጉ የመውረድ ዕጣ ፈንታ ቢያጋጥመውም የትግራይ ክልል ክለቦችን በመተካት በተደረገው ውድድር ዳግም የመትረፍ ዕድል አግኝቶ በሊጉ መሰንበቱ ይታወቃል። ይህ ቢሆንም ግን በዘንድሮ የውድድር ዓመት ካለፉት ዓመታት በባሰ የሜዳ እና የሜዳ ውጪ ችግሮቹ ተተብትቦ ማግኘት ከሚገባው 27 ነጥቦች አንዱን ብቻ አሳክቶ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።
በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ክለቡ ሊጉ የ9 ሳምንታት ጉዞን አድርጎ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲቋረጥ ለተጫዋቾቹ የ15 ቀናት የእረፍት ጊዜ ሰጥቶ ነበር። ከዛም ተጫዋቾቹ ከጥር 1 ጀምሮ ለቀጣይ የሊጉ ምዕራፍ ዝግጅት እንዲያደርጉ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም እቅዱ ተግባራዊ እንዳልሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።
የሦስት ወራት የተጫዋቾች ደሞዝ መክፈል እንዳልቻለ የሚገለፀው ጅማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከተመለሰ ከ5 ቀናት በኋላ ለሚጀምረው የሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ውድድር ራሱን ማዘጋጀት እንዳልጀመረ መስማት እጅግ አስገራሚ ሆኗል። ጉዳዩን በተመለከተ የክለቡን አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለማንሳት ባይሳካም ከገንዘብ ጋር በተፈጠረ ችግር እንደሆነ ሰምተናል። ለተጫዋቾች ከሚሰጥ ያለፉት ወራት ደሞዝ ውጪም ዝግጅት ለመጀመር የሆቴል እና ተያያዥ ወጪዎችን የሚሸፈኑበት ገንዘብ እስካሁን ባለመገኘት እንደሆነ ተረድተናል።
ከክለቡ አንዳንድ ተጫዋቾች ጋር ባደረግነው ቆይታም ተጫዋቾቹ ባለው ነገር ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልፀው በህብረትም ሆነ በተናጥል ወደ ክለቡ አመራሮች ስልክ ሲደውሉ እንደማይነሳላቸው አስረድተውናል። ክለቡ ካለበት ደረጃ መነሻነትም ሥራዎች ቀድመው መሰራት ሲገባቸው ከሌሎች ክለቦች በተቃራኒ ዝምታ ተመርጦ መቀመጣቸው በቀጣይ ጨዋታዎች ላይም ተፅዕኖ እንደሚፈጥርባቸው ስጋት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ከላይ እንደገለፅነው የክለቡ አመራሮችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም በቀጣይ ምላሾች የሚሰጡን ከሆነ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።