ኢትዮጵያ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ነጥብ በተጋራችበት ጨዋታ ኮከብ በመባል የተመረጠው አማኑኤል ዮሐንስ በድጋሚ በሌላ የኮከብነት ምርጫ ላይ ዕጩ ሆኗል።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ አንድ ነጥብ ብቻ በመያዝ በጊዜ ተሰናባች መሆኑ ይታወቃል። ባሳለፍነው ሰኞ ባፉሳም ከተማ የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ከቡርኪናፋሶ ጋር ያከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምንም እንኳን በጨዋታው ድል ባይቀናውም በጌታነህ ከበደ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ነጥብ መጋራቱ ይታወሳል። በዕለቱም በካፍ የቴክኒክ ኮሚቴ የጨዋታ ኮከብ በመባልም አማኑኤል ዮሐንስ መመረጡም አይዘነጋም።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ የካፍ ቴክኒክ ኮሚቴ የምድብ ጨዋታዎች ላይ ጎልተው የወጡ ምርጥ አስራ አንድ ተጫዋቾችን በሚመርጥበት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያዊው አማካይ አማኑኤል ዮሐንስ ስም በዕጩ ዝርዝር ውስጥ መካተቱን አረጋግጠናል።
ዛሬ ምሽት አልያም ነገ ይፋ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የምርጥ አስራ አንድ ሙሉ ስም ዝርዝር መረጃ እንደደሰረሰን የምናቀርብ ይሆናል።