ምሽት ላይ በተካሄደው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ባህር ዳርን ከረታ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
በሁለተኛው አጋማሽ ስላደረጉት የተለየ እንቅስቃሴ
ውጤቱ እንቅስቃሴያችንን ነው የሚገልፀው። በጎል ተቀድመን ነበር። ስለዚህ የግድ ማግባት ነበረብን። ሁለት ጎል ማግባት ቀላል አይባልም። እንደ እንቅስቃሴያችን ውጤቱ ይገባናል። ዛሬ ይዘነው የመጣነው የጨዋታ ፍልስፍና ወደ ኃላ በመሆን በፈጣን እንቅስቃሴ እያጠቁ ማሸነፍ ነበር። ሦስት ነጥብ የግድ ዛሬ ያስፈልገን ስለነበር፤ በዚህ ውስጥ መጀመርያም ቢሆን የተቀደምነው የራሳችንን ጨዋታ አሳልፈን ስለሰጠን ነው። ከእረፍት በኃላ ይህ ቁጭት ነበር። ስለዚህ ተግባራዊ አድርገውታል በጣም ጥሩ ነው።
የማሸነፋቸው ትርጉም በምን ይገለፃል?
እውነት ነው። ለምን ከነበርንበት የውጤት ቀውስ አንፃር ከዛ ለመውጣት በምናደርገው ሽግግር ውጤቱ ቀላል አይደለም። ቀላል የሚባል አይደለም የገጠመን ፈተና ስለዚህ ያለፉት ሁለት ጨዋታ የዛሬን ጨዋታ ጨምሮ ስድስት ነጥብ አግኝተናል። ይህ ብዙ ነው ከዛ በፊት በተከታታይ ስድስት ነጥብ ማግኘት አይደለም ሦስት ነጥብ ማግኘት ከባድ ነበር። የነበሩብን ጨዋታዎች በሙሉ ከባዶች ነበሩ። አሁን የተሻለ ጥሩ ነገር ይዘናል ብዬ ነው የማስበው። ትንሽ ወደ ፊት ለመሄድ ለመቀራረብ ዕድሉ ተመቻችቷል ስለዚህ ከዚህ በኃላ ጥሩ እንሆናለው ብዬ አስባለው።
ምክትል አሰልጣኝ አብርሀም መላኩ – ባህር ዳር ከተማ
የተጫዋቾች ጉዳት ተፅዕኖ
አዎ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ተናግሬ ነበር። ልጆቻችን ላይ ጉዳት እንዳለ ጭራሽ ደግሞ ጨዋታው እየሄደ መናፍን ማጣታችን ሌላ አማራጭ እንድንጠቀም አደረገን። የመጀመርያው አማራጭ የተሻለ ነበር ጎል ያገኘንበት የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርግንበት ነበር ጉዳቱ ጨዋታችንን ወደ ማንፈልግበት መንገድ እንዲሄድ አድርጎታል።
የሜዳው ሁኔታ
ሜዳው በጣም ጥሩ ነው። ትንሽ ጉልበት የሚፈልግ እንደሆነ ያስታውቃል። ሳሩ ያልታጨደ ስለሆነ ጉልበት ይፈልጋል በዚህም ልጆቻችንን ትንሽ ፈትኗቸዋል።