ነገ በሚከናወኑት ሁለቱ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ወልቂጤ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
ከመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቻቸው ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት ያገኛቸው ሁለቱ ተጋጣሚዎች በሀዋሳ የነበራቸውን መልካም አጨራረስ በድሬዳዋ ለማስቀጠል ይገናኛሉ።
በሊጉ ደካማ አጀማመር አድርገው የነበሩት ወልቂጤዎች አሁን ላይ ከመሪዎቹ ተርታ ተሰልፈዋል። እስካሁን አራት ድል ያስመዘገቡት ሰራተኞቹ አምና በነበረው ስብስባቸው ላይ ስር ነቀል ለውጥ አለማድረጋቸው የጠቀማቸው ይመስላል። ሆኖም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ዘላቂ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አሁንም ተደጋጋሚ ድሎችን ማስመዝገብ ያስፈልጋቸዋል። በሊጉ ግርጌ ለመሰንበት ተገዶ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ከነገ ተጋጣሚው ዘግየት ብሎ ነበር ነፍስ የዘራው። ሀዲያዎች በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቻቸው ያሳኳቸው ዘጠኝ ነጥቦች ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ አስጠግተዋቸዋል። ያም ሆኖ ከወረጅ ቀጠናው አስተማማኝ የነጥብ ልዩነት ለመፍጠር እና ወደ ላይ ከፍ ለማለት ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት አስፈላጊያቸው ነው።
ወልቂጤ ከተማ በፊፋ የታገደው ግብ ጠባቂው ሲልቪያን ግቦሆን ጨምሮ ጉዳት ላይ የሚገኘውን አቡበከር ሳኒን የሚያጣ ሲሆን እስራኤል እሸቱ እና አብዱልከሪም ወርቁም መጠነኛ ጉዳት አግኝቷቸዋል። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ አስቻለው ግርማ እና መላኩ ወልዴ በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት የሌሉ ሲሆን የኤፍሬም ዘካሪያስ መሰለፍም እርግጥ አይደለም።
ለዚህ ጨዋታ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት ክንፈ ይልማ እና ሶርሳ ድጉማ በረዳትነት ዳንኤል ግርማይ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውለታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኙባቸው የዓምናዎቹ ጨዋታዎች የመጀመሪያው 1-1 ሲጠናቀቅ ሁለተኛውን ሀዲያ ሆሳዕና 2-0 ማሸነፍ ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ፋሲል ከነማ
በሳምንቱ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ከፍ ያለ ግምት የተሰጠው እና በዋንጫ ተፎካካሪዎቹ መካከል የሚደረገው ይህ ጨዋታ ትኩረትን የሚስብ ነው። በእርግጥም የዚህ ጨዋታ ባለ ድል የዘንድሮውን ዋንጫ ለማንሳት ድሬዳዋ ላይ ሊሰበስብ የሚያልማቸውን ነጥቦች ለማግኘት ጥሩ ጅምር ይሆንለታል።
እስካሁን ሽንፈት ያላገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ ጠንከር ብሎ የመጣ ይመስላል። ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ውጪ በሰፊ ልዩነት ተጋጣሚዎቹን መርታት ባይችልም የሰበሰባቸው ነጥቦች በፉክክሩ ውስጥ አቆይተውታል። ዘንድሮም የአሰልጣኝ አለመረጋጋት የገጠመው መሆኑ ይህንን ተከትሎም ውድድሩ ጥቂት እንደሄደ ለውጦችን ለማድረግ ያስገደደው ከመሆኑ አንፃር ሲታይ የጊይርጊስ የሀዋሳ አፈፃፀም ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል። ቻምፒዮኖቹ ፋሲሎች ደግሞ በሦስት ተከታታይ ድሎች በጀመሩት የዘንድሮው ውድድር በጊዜ ርቀው የመሄድ ምልክት ቢያሳዩም ባልተጠበቁ ጨዋታዎች ነጥቦችን መጣላቸው ተፎካካሪዎቻቸው እንዲጠጓቸው አድርጓል። በድሬዳዋ ቆይታቸው ከሀዋሳው በተሻለ የትኩረት ደረጃ ክብራቸውን ለማስጠበቅ እንደሚፋለሙም ይጠበቃል።
በነገው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አዲስ ግደይ እና ሀይደር ሸረፋ በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ሲሆን ፋሱል ከነማዎች ግን ከጉሳት እና ቅጣት ነፃ ሆነው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በዋና ዳኝነት ሲመሩት ትግል ግዛው እና ካሳሁን ፍፁም በረዳትነንት ባህሩ ተካ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለት ፎርፌዎችን ጨምሮ እስካሁን በሊጉ ዘጠኝ ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ዕኩል 11 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ፋሲል ከነማ አራት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሦስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል።