ከአስረኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ሙለጌታ ምህረት -ሀድያ ሆሳዕና
ስለጨዋታው
“ጨወታውን እንዳየኸው ሁለት መልክ ነው ያለው ፤ ከዕረፍት በፊት ጥሩ ነበርን፡፡ ከዕረፍት በኋላ ደግሞ ትንሽ ወደ ኋላ ሸሽተን በመጫወታችን አቻ ሆነን ለመውጣት ተገደናል። በጨዋታው የመጀመሪያ ቀን ላይ በመሆናችንም ዘጠኝ ሰዓት ሞቃታማ በመሆኑ ተመጣጣኝ ነው ብዬ የማስበው፡፡
በተጫዋችነት አንድ ቢጫ ዛሬ በአሰልጣኝነት አንድ ቢጫ ስለማግኘቱ
“ስለዳኛ ማውራት ያው አያስፈልግም። አጋጣሚ ተናድጄ ሀይላንድ ነው የመታውት ከእነርሱ ጋርም የሚያገናኝ አልነበረም። ግን ያው ዞሮ ዞሮ እነሱ ያዩት እና ሜዳ ውስጥም የተመለከቱት ስለሆነ ተቀብያለሁ፡፡
ስለ ውጤቱ
“እንደ መጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃችን ከዕረፍት በኋላ ከነበረው የተሻለ ነበረ እና ይዘን በደንብ አስጠብቀን መውጣት እንችል ነበር፡፡ አሁንም በዚህ ጨርሰን መውጣት እንችል ነበር፡፡ በራሳችን ስህተት ስለሆነ ስህተቱ ይሄ የእግር ኳስ አንዱ ባህሪ ስለሆነ እንቀበላለን፡፡
ስለቀጣዮቹ ጨዋታዎች
“ምንም ነገር የለም ሁሌም ስራ ላይ ነን። ለቀጣዩ ጨዋታ ደግሞ አሁን ያጣናቸውን ክፍተቶቻችን ላይ ሰርተን የምንመለሰው፡፡
አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ
ስለ ውጤቱ
” ያው ውጤቱ ባያስከፋኝም ከዕረፍት በፊት በነበረን እንቅስቃሴ ጥሩ አልነበርንም መሀል ሜዳም ብልጫ ተወስዶብን ነበረ፡፡ ያም ነገር እንግዲህ ውድድሩ ከተቋረጠ በኋላ የመጀመሪያችን ነው፡፡ ስህተቶቻችን እያረምን እንመጣለን። ከዕረፍት በኋላ እንደተመለከታችሁት ስህተቶችን አርመን ብዙ ጊዜ ጎል ጋር ደርሰናል መጨረሻ ላይ ባገባነው ጎል አቻ ወጥተናል በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
በመልበሻ ቤት ምን ተነጋገራችሁ
“ከዚህ በፊትም የኔ ቡድን አጥቅቶ መጫወት የሚችል ቡድን ነው፡፡ ኳሊቲ ያላቸው ተጫዋቾችም ናቸው። በተለይ ወደፊት መሄድ የሚችሉ አቅም ያላቸው ልጆች ቤንችም ላይ የተቀመጡ ልጆች ብዙ አሉ። ስለዚህ አጥቅተን እንደምንጫወት ሁልጊዜ ግልፅ ነው ከማንም ከአስራ አምስቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቡድኖች በተሻለ ወደፊትም ጠብቁ ስንጫወት አጥቅተን ነው የምንጫወተው እና የተቆጠሩን ጎሎች በራሳችን ስህተት ነው፡፡ የተከላካዮች መዘናጋት ነው፡፡ለተቃራኒው ክፍተት በመስጠታቸው የመጡ ናቸው። በቀጣዩ ጌም አርመን ጥሩ ተወዳዳሪ እና ለዋንጫም ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን እስከ መጨረሻው እንሰራለን፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ ስላልተሰጣችሁ ፍፁም ቅጣት ምት
“እኔ ያ የዳኛ ስራ ስለሆነ እዛ ውስጥ መግባት አልፈልግም።”