አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን በመንበሩ የሾመው መቻል ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ሲቀላቅል የአንድ ነባር ተጫዋቹንም ውል አራዝሟል።
በቀጣዩ የውድድር ዓመት አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን በዋና አሠልጣኝነት እንዲሁም ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱን በቴክኒክ አማካሪነት ወደ ክለቡ ያመጣው መቻል ከቀናት በፊት የምንተስኖት አዳነ እና በኃይሉ ግርማን ውል ያራዘመ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ወደ ዝውውር መስኮቱ በይፋ በመግባት የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቆ የአንድ ነባር ተጫዋች ውል አድሷል።
ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች አቤል ነጋሽ ነው። ዓምና እና ዘንድሮ በአዲስ አበባ እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ ያሳለፈው የመስመር አጥቂው በሁለት ዓመት ውል ዳግም የመቻልን መለያ የሚለብስበትን ውል ፈርሟል።
ሁለተኛው ተጫዋች ነስረዲን ኃይሉ ነው። የቀድሞ የለገጣፎ ለገዳዲ ተጫዋች ዓምና ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን ግልጋሎት ሳይሰጥ በስምምነት ተለያይቶ ዓመቱን በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ገላን አሳልፏል። እርሱም እንደ አቤል ወደ ቀድሞ ክለቡ በአንድ ዓመት ውል ተዘዋውሯል።
ውሉን ያደሰው ተጫዋች ደግሞ ግርማ ዲሳሳ ነው። ረዘም ላሉ ዓመታት በባህር ዳር ከተማ ከተጫወተ በኋላ ዓምና ወደ መቻል የመጣው ሁለገቡ የመስመር ተጫዋች በክለቡ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል።