የናይጄርያ እግርኳስ ፌደሬሽን ከጭልፊቶቹ እና ሉሲዎቹ ጨዋታ ጋር በተያያዘ ለደጋፊዎቹ ጥሪ አቅርቧል።
ለፓሪሱ የ2024 ኦሊምፒክ ማጣርያ ከሉሲዎቹ ጋር ታደልድለው በመጀመርያው ጨዋታ አቻ ተለያይተው የመልሱን ጨዋታ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት
የ11 ጊዜ የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮኖቹ
ናይጀርያዎች በነገው ዕለት በሚካሄደው ጨዋታ ደጋፊዎች ካለ ክፍያ በነፃ እንዲገቡ ወስነዋል።
ኤግል 7 የተሰኘው የሀገሪቱ ራዲዮ የፌደሬሽኑን የበላይ አመራር ሳኑሲ መሐመድ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ ፌደሬሽኑ ደጋፊዎች ስታዲየሙን ሞልተው ጭልፊቶቹን እንዲደግፉ ታሳቢ አድርጎ ይህንን ውሳኔ እንደወሰነ ገልፀዋል። የብሔራዊ ቡድኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቶቤ ቹኩው በበኩላቸው ደጋፍያቸው በአውስትራልያው የዓለም ዋንጫ ለነበረው አበርክቶ አመስግነው ብሔራዊ ቡድኑ ከአስራ አምስት ዓመታት በኋላ ለኦሊምፒክ የሚያበቃውን ውጤት እንዲያስመዘግብ ሁሉም ስታዲየም ገብቶ ከጭልፊቶቹ ጎን እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል።
በተያያዘ ዜና 35 ልዑካንን ያካተተው የሉሲዎቹ ስብስብ በሰላም አቡጃ የደረሰ ሲሆን የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ በሦስተኛው ዙር የማጣርያ ጨዋታ ከዩጋንዳ እና ካሜሩን አሸናፊ ጋር የሚገጥም ሲሆን ዛምቢያ እና ቱኒዝያ ደግሞ ተጋጣሚዎቻቸው ኮትዲቯዋር እና ማሊ ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ ቀድመው ወደ ሦስተኛው ዙር ማለፋቸው ያረጋገጡ ቡድኖች ሆነዋል።
ተጠባቂው የኢትዮጵያና ናይጄርያ ጨዋታ በነገው ዕለት በMKO Abiola ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል።