በዕለቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር አዳማ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 2-1 ረቷል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ሲገናኙ ድሬዎች በንግድ ባንክ ሲረቱ የነበረውን ስብስብ ሳይለውጡ ለዚህ ጨዋታ ሲቀርቡ አዳማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ከወጡበት መርሐግብራቸው በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል። ኤልያስ ለገሠ እና መስዑድ መሐመድ አርፈው በቻርለስ ሪቫኑ እና ቢኒያም አይተን ተተክተዋል።
ቀን 9 ሰዓት በጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታውን የመጀመሪያ ንጹህ የግብ ዕድል ድሬዳዋዎች መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም አቤል አሰበ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ኤፍሬም አሻሞ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በተደራጀ እና ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጋጣሚን የግብ ክልል መፈተን የጀመሩት አዳማዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቻርለስ ሪባኑ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ እየገፋ በሳጥኑ የግራ ክፍል ውስጥ የደረሰው አብዲሳ ጀማል በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። አዳማዎች በአንድ ደቂቃ ልዩነትም በዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።
ከሩብ ደቂቃዎች በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት ድሬዳዋዎች 28ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ኤልያስ አህመድ በሳጥኑ የግራ ክፍል በግሩም ክህሎት ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ ሳያገኘው ቀርቶ ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሄዶ በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ወደ ዕረፍት ሊያመሩ ሲል በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ ድሬዎች በድጋሚ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ነጻ ሆኖ ያገኘው አቤል አሰበ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ የኳሱ ኃይል-የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ በቀላሉ ይዞበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታውን በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት ብርቱካናማዎቹ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ግብ ሊያስቆጥሩ ነበር። አብዱለጢፍ መሐመድ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ሲያሻማ ኳሱ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ግብ ሄዶ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።
ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ድሬዎች በርካታ ንጹህ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም እጅግ ደካማ በሆነ አጨራረስ አባክነውታል። በተለይም 56ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኳስ ይዞ የገባው አቤል አሰበ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበት ብርቱካናማዎቹን አስቆጭቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ተቀዛቅዘው የቀረቡት አዳማዎች በአጥቂ ክፍላቸው ላይ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ ነፍስ ዘርተውበት 64ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ዮሴፍ ታረቀኝ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ሲመልስበት የተመለሰው ኳስ የድሬውን የመስመር ተከላካይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ገጭቶ ግብ ሆኗል። አዳማዎች በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም በዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት ከቅጣት ምት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።
የፈጠሯቸውን በርካታ የግብ ዕድሎች ባለመጠቀማቸው የራስ መተማመናቸውን ያጡት ብርቱካናማዎቹም እየተቀዛቀዙ ሄደው በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች በመጠኑ ወደ ነበራቸው ግለት ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን 82ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ አህመድ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ከመለሰው ኳስ ውጪ ተጨማሪ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግረው ሲታዩ 95ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተቀይሮ የገባው ዘርዓይ ገብረሥላሴ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ለዜሮ ከመሸነፍ አድኖት ጨዋታው እንቅስቃሴውን በሚፈልጉት ሂደት ባስኬዱት አዳማ ከተማዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።