ሪፖርት | አዳማ እና ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

10:00 ላይ የተደረገው የአዳማ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

ተጋጣሚዎቹ ከመጨረሻ ጨዋታቸው ባደረጓቸው ተመሳሳይ ለውጦች የአዳማዎቹ ዮሴፍ ዮሐንስ እና አሜ መሀመድ በታደለ መንገሻ እና አብዲሳ ጀማል ሲተኩ ወንድሜነህ ደረጄ እና ሮቤል ተክለሚካኤል ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በቴዎድሮስ በቀለ እና ዊሊያም ሰለሞን ቦታ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታው በጥሩ ፉክክር ቢጀምርም በሁለቱም በኩል የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ከባድ ሆኖ ታይቷል። በተለመደው አኳኋን ቅብብሎችን እየከውኑ አንዳንዴም ከተከላካይ ጀርባ ኳስ ለመጣል እየሞከሩ የታዩት ቡናዎች አዳማን አስከፍተው ለመግባት ተቸግረዋል። አዳማዎችም ቡናን ከኳስ ውጪ በመጫን ኳሶችን እያቋረጡ ፈጣን ጥቃቶችን ለመፈፀም ሞክረዋል። የቡድኑ ወደ ግራ መስመር ያደላ ጥቃት ግን አልፎ አልፎ ጥሩ ምልክት ቢያሳይም ከቡና የመከላከል አቅም በላይ መሆን አልቻለም።


ከውሀ ዕረፍቱ መልስ ኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይበልጥ ማጠናከር ቢችልም ወደ ተጋጣሚው ሳጥን መጠጋት ግን አልሆነለትም። ኳሶችን በማቋረጡ የተሳካላቸው አዳማዎችም ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር ደካማ  እየሆነ በብዛት በሜዳቸው ለመቆየት ተገደዋል። በዚህ ረገድ ጥሩ እምርታ ባሳዩበት 37ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው አብዲሳ ጀማል ካቋረጠው  የአየር ላይ ኳስ መነሻነት ለዳዋ ሆቴሳ ጥሩ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ያደረሰበት አጋጣሚ የጨዋታው አደገኛ ዕድል ቢሆንም ዳዋ ፈጥኖ ከወጣው አቤል ማሞ ጋር ተጋጭቶ ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል። ቡናዎች አጋማሹ ሊያበቃ ሲቃረብ እንዳለ ደባልቄን ያማከሉ ቅብብሎቻቸው በተሻለ ሁኔታ ለጀማል ጣሰው ክልል ቀርበው ቢታዩም ቀዝቃዛው ጨዋታ ያለ ጎል መጋመሱ አልቀረም።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ቡናዎች ከዕርፍት በፊት የጀመሩት ጫና እየጎላ መጥቷል። ቡድኑ ይበልጥ ወደ አዳማ ሳጥን ተጠግቶ ማስጨነቅ ሲጀምር አዳማዎች ይበልጥ ወደ ኋላ ተስበው በመልሶ ማጥቃት የሚወጡበትን አጋጣሚ ይጠባበቁ ነበር። ከቡና ጫና መነሻነት 58ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ ከግራ ያሻማውን ኳስ  እንዳለ ደባልቄ አመቻችቶለት በቀኙ ቋሚ በጠበበ ቦታ ላይ አቤል እንዳለ ያደረገው የጨዋታው የመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ በጅማል ጣሰው ድኗል። አዳማዎች አልፎ አልፎ ፈጥነው ወደ ቡና ሜዳ ለመግባት ሲጥሩ የቅብብል ስኬታቸው መውረድ ለዳግም ጥቃት ሊያጋልጣቸው ሲቃረብ ታይቷል። በተለይም 67ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበት ቢያገኙም ኳስ ተነጥቀው ቡናዎች ለእንዳለ ደባልቄ  የላኩትን ረዘም ያለ ኳስ አጥቂው ሲያስቀርለት ታፈሰ ሰለሞን ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ወደ ላይ ተነስቶበታል።

ከሁለተኛው ውሀ ዕረፍት መልስ አዳማዎች ተቀይሮ የገባው ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ በመታው እና ሮቤል ተክለሚካኤል በተደረሰበት ኳስ ወደ ሙከራ መጥተዋል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም አዳማዎች የማጥቃት የበላይነቱን መውሰድ ሲችሉ የቡና የኳስ ቁጥጥር ተቀዛቅዞ ታይቷል። ወደ ፍፃሜው ሲቃረብ ወደ መቀዛቀዙ የተመለሰው ጨዋታ ግን ግብ ሳይቆጠርበት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ተጋጣሚዎቹ  አንድ አንድ ነጥብ ሲካፈሉ አዳማ ከተማ ወደ  5ኛ ኢትዮጵያ ቡና ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል።