በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በኢዮብ ዓለማየሁ ብቸኛ ግብ ሲዳማ ቡናን 1-0 መርታት ችሏል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ መካከል የሚደረገው የሮዱዋ ደርቢ ጨዋታ ሲደረግ ሲዳማ ቡና ከሻሸመኔው ድላቸው አበባየሁ ዮሐንስ እና አቤኔዘር አስፋውን አስወጥተው ሙሉቀን አዲሱ እና ቡልቻ ሹራን ሲተኩ ሀዋሳዎች በመድኑ የተጠቀሙትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም የመጨረሻ ኳሳቸው ፈታኝ አልነበረም። የጨዋታው የመጀመሪያ የተሻለ ሙከራም 13ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የኃይቆቹ አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ሲዳማዎች 20ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት እዛው ተቀባብሎ በመጀመር እና ወደ ግብ በመምታት ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ከሩብ ደቂቃዎች በኋላ ባሉት 10 ደቂቃዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ሀዋሳዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ሙጅብ ቃሲም ከፍ አድርጎ በመምታት ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ኢዮብ ዓለማየሁ ያደረገውን ሙከራ የመስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሐንስ በድንቅ ቅልጥፍና ተደርቦ አግዶበታል።
አማካይ ክፍላቸው ላይ ቢጫ ካርድ የተመለከተውን ዮሴፍ ዮሐንስን አስወጥተው በዛብህ መለዩን ያስገቡት ሲዳማዎች በጥሩ የኳስ ቅብብል 40ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን ፈጥረው ነበር። ደስታ ዮሐንስ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ገዛኸኝ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ በቀላሉ ይዞበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል ሲዳማዎች ባልታሰበ አጋጣሚ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው ነበር። ተከላካዮች በሠሩት ስህተት ኳስ ያገኘው ቡልቻ ሹራ ተከላካይ ለማለፍ ሲሞክር ተቀምቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም ደስታ ዮሐንስ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋችም ሆነ የአደራደር ለውጥ ያደረጉት ኃይቆቹ በተሻለ እንቅሰቃሴ የጨዋታውን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ 54ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ የሲዳማ ተከላካዮች የመለሱትን ኳስ ያገኘው ኢዮብ ዓለማየሁ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ በግሩም ቅልጥፍና መልሶበታል።
ጨዋታው 65ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። መድኃኔ ብርሃኔ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ኢዮብ ዓለማየሁ የተቆጣጠረውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ግብ በተቆጠረባቸው ቅፅበት መልስ ለመስጠት በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው የተጫወቱት ሲዳማዎች በአጋማሹ የተሻለ ሙከራቸውን 71ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ቡልቻ ሹራ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ አክርሮ በመምታት ያደረገው ጥሩ ሙከራ በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉካጎ ተጨርፎ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ጨዋታው መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳያስመለክተን በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።