👉”በሞሮኮ በሚኖረን ቆይታ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስፖርት መሰረት ልማቶችን እና በቆይታችን የሚኖሩ ወጪዎችን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍንልን ይሆናል።”
👉”በአጠቃላይ በሜዳችን ለምናደርጋቸው 5 ጨዋታዎችን በ180,000 የአሜሪካን ዶላር የማርኬቲንግ መብቱን ሸጠናል።”- አቶ ባህሩ ጥላሁን
ዛሬ ረፋድ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በይፋ የወንዶች ዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው መቀጠራቸው ይፋ በተደረገበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ስለሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች በፌደሬሽኑ የፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በኩል ማብራሪያ ተሰጥቷል።
አቶ ባህሩ በቀጣይ ቡድኑ በሞሮኮ ስለሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ይህን ብለዋል
“ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎቻችን በሞሮኮ አል አብዲ ስታዲየም የሚደረጉ ይሆናል ፤ በህዳር 5 እና በህዳር 11 የሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ናቸው። በሞሮኮ በሚኖረን ቆይታ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስፖርት መሰረት ልማቶችን እና በቆይታችን የሚኖሩ ወጪዎችን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍንልን ይሆናል።በነገራችን ላይ እንደ እኛ ሁሉ ሌሎች በርከት ያሉ ደረጃውን የሚያሟላ ስታዲየም የሌላቸው ሀገራት ጨዋታቸውን በሞሮኮ የሚያደርጉ ይሆናል።ይህንንም ማድረግ የቻለነው ከዚህ ቀደም በተፈራረምነው የመግባቢያ ሰነድ እና በክቡር ፕሬዝዳንታችን በስፖርት ዲፕሎማሲ ረገድ በተደረገ ጥረት የተገኘ ስኬት ነው።በዚህ አጋጣሚም የሞሮኮን እግር ኳስ ፌደሬሽንን ለማመስገን እንወዳለን።”
በማብራሪያቸው ፌደሬሽኑ በቀጣይ የአለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ዙርያ ከአንድ ተቋም ጋር ስላለሰረው ውል ስምምነትም ተከታዩን ነጥብ አንስተዋል።
“እንደ ፌደሬሽን ደግሞ በማርኬቲንግ ዘርፍ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ስፖርት ኤጅ ከተሰኘ ተቋም ጋር አምስት በሜዳችን የምናደርጋቸው የአለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎችን የማርኬቲንግ መብት ሸጠናል። በዚህ ረገድ ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ተቋማት ነበሩ ነገርግን ፍላጎታቸው የነበረው ከግብፅ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ላይ ነበር።ይህ ጨዋታ ከእግር ኳሳዊ ጉዳዮች ባሻገር ጨዋታው ባለዌፈው ትርጉም ትልቅ የማርኬቲንግ አቅም እንዳለው ይታወቃል ባለፈው ማላዊ ላይ ከግብፅ ጋር ያደረግነው ጨዋታ ትልቅ የማርኬቲንግ ገቢ ያገኘንበት እንደነበርም ይታወቃል አሁን ላይ ይህ ተቋም ምንም እንኳን በይበልጥ የግቡፁን ጨዋታ ቢፈልገውም ሌሎችንም ጨዋታዎች መብት እንዲገዙ ማግባባት ችለናል።በአጠቃላይ በሜዳችን ለምናደርጋቸው 5 ጨዋታዎችን በ180,000 የአሜሪካን ዶላር የማርኬቲንግ መብቱን ሸጠናል።የግብፁ ጨዋታ በተናጥል 140,000 የአሜሪካ ዶላር የማርኬቲንግ መብቱ ሲሸጥ የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በ40,000 ዶላር ተሸጠዋል።”
“መሰል አማራጮችን ከዚህ በኃላ ለመጠቀም እየሞከርን ነው የምንገኘው ምንም እንኳን ገንዘቡ ከጨዋታዎቹ በኃላ ገቢ የሚደረግ ቢሆንም በማርኬቲንግ ረገድ 180,000 የአሜሪካን ዶላር የማርኬቲንግ መብት መሸጣችንን ለማሳወቅ እንወዳለን።”