በትናንትናው ዕለት የዋልያዎቹ ዋና አሠልጣኝ በመሆን የተሾሙት ገብረመድህን ኃይሌ ምክትሎቻቸውን ይፋ አድርገዋል።
ያለፉትን ወራት በጊዜያዊ አሠልጣኝ ሲመራ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትናንትናው ዕለት አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን በቋሚነት ማግኘቱ ይታወቃል። አሠልጣኙ አመሻሽ ላይ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ከፊታቸው ላለባቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅታቸውን ከመጀመራቸው አንድ ቀን አስቀድሞ ደግሞ ረዳቶቻቸውን ለይተዋል።
በዚህም አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ የብሔራዊ ቡድኑ ረዳት አሠልጣኝ በመሆን መመረጣቸው ታውቋል። የቀድሞ የወላይታ ድቻ፣ ፋሲል ከነማ እና አርባምንጭ ከተማ አሠልጣኝ የነበሩት መሳይ ዓምና የሊጉ የመገባደጃ ሳምንታት ላይ ከአዞዎቹ ጋር ከተለያዩ በኋላ ያለ ኃላፊነት ተቀምጠው የነበረ ሲሆን አሁን የዋልያዎቹ ረዳት በመሆን የአንድ ዓመት ውል ፈርመዋል።
የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ በመሆን ደግሞ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ዘመን የግብ ዘቦች አሠልጣኝ የነበረው አሠልጣኝ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ዳግም ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ተመልሷል።