በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚካፈለው ወሎ ኮምቦልቻ የአስራ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ቋጭቷል።
በ2016 የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ በመደልደል ውድድሩን የሚያከናውነው ወሎ ኮምቦልቻ ራሱን በተሻለ ተፎካካሪነት ላይ ለመገኘት በማሰብ ከሳምንታት በፊት አሰልጣኝ ደረጀ በላይን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረ ሲሆን በዝውውሩ በመካፈል በርካታ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባሮችን ውልም አድሷል።
አዲሶቹ ፈራሚዎች ግብ ጠባቂዎቹ ታደሰ ያለዉ እና ሠለሞን ደምሴ በተከላካይ ስፍራ የሚጫወቱት ብኛክ ኬር ፣ ፋንታሁን ተስፋዬ ፣ እስራኤል ዘርፉ ፣ ብሩክ ግርማ እና አሌክስ ብርሀኑ አማካዮቹ ተካልኝ መስፍን ፣ ኢምራን ሱለይማን ፣ ሰዒድ ግርማ እና ተመስገን ታምራት የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ማኑሄ ጌታቸው ፣ መልካሙ ፉንዱሬ ፣ ዮሐንስ ኪሮስ እና ኦኒ ኡጁሉ ናቸው።
ክለቡ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ የቃልፍቅር መስፍን ፣ ሄኖክ ከበደ ፣ ጀማል አሊ ፣ ሄኖክ ጥላሁን ፣ ሠለሞን ሀብቱ ፣ ኤፍሬም አሰፋ ፣ ሳሙኤል በለጠ እና ዮናታን ኃይሉን ውል አራዝሟል።
ወሎ ኮምቦልቻ ነገ በሀዋሳ 08:00 ላይ ነጌሌ አርሲን በመግጠም የውድድር ዓመቱን ይጀምራል።