[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የ12ኛው ሳምንት መቋጫ በሆነው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
በጥሩ ወቅታዊ ውጤቶች ላይ የሚገኙት የነገ ምሽት ተጋጣሚዎቹ ጅማ እና ሲዳማ የጨዋታ ሳምንቱን ዓይን በሚስብ ፉክክር እንደሚዘጉት ተስፋ ይደረጋል። የዓመቱ ቀዳሚ ድላቸውን በሁለተኛ ድል ያጎለበቱት ጅማዎች አሸንፈው የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌውን ለሰበታ ለማስረከብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ላለፉት አራት ጨዋታዎች ሽንፈትን አስወግደው ስምንት ነጥቦችን ያሳኩት ሲዳማዎችም በቶሎ ከታችኛው የደረጃ ክፍል ሲጠበቁበት ወደነበረው የላይኛው ፉክክር ለመሻገር ነጥቦቹ ያስፈልጓቸዋል።
ይህ ጨዋታ አማካይ ክፍል ላይ በሚኖረው ፍልሚያ የሚወሰን ይመስላል። ቡድኖቹ በቅርብ ባደረጓቸው ጨዋታዎች የመሀል ክፍል ተጫዋቾቻቸው ለግብ መነሻ ሲሆኑ መታየታቸው እና የተጨዋቾቹ ቦታ አያያዝ ፍልሚያውን ሳቢ ሊያደርገው ይችላል። በሽግግሮች ወቅት የሚኖሩት የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችም ለተጋጣሚዎቹ አጥቂዎች የመጨረሻ ዕድል ለመፍጠር አልያም የባላጋራን የምስረታ ሁደት በማቋረጥ የሚኖራቸው ሚና መጉላቱ የሚቀር አይመስልም።
ወደ መልካም ውጤት የመጣው ጅማ አባ ጅፋር የሚመጥነውን የማጥቃት አማራጭ ያገኘ ይመስላል። ባለልምድ የሆኑት ዳዊት እና መስዑድ እንዲሁም ታታሪው በላይ አባይነህ አማካይ ክፍል ላይ ያላቸው ሚና ረጅም ሰዓት የኳስ ቁጥጥርን ለማግኘት ካለው አበርክቶት በላይ የማጥቃት መስመሮችን በመወሰን እና ወሳኝ ኳሶችን በቶሎ ወደ ፊት በመላክ ላይ እየጎላ መጥቷል። ይህ የጅማ ጠንካራ ጎን በመሀመድኑር ናስር እና እና እዮብ ዓለማየሁ ፍጥነት ሲታገዝ ቡድኑን ከፊት ስል እያደረገው ይገኛል። በነገው ጨዋታ ይህንን እንድንመለከት ግን አማካይ የቦታ አያያዙ ወደ ራሱ ሜዳ የተጠጋው እና በቁጥር ከሚመጣጠናቸው የሲዳማ መሀል ክፍል የኳስ ውጪ እንቅስቃሴ በልጠው መገኘት ይኖርባቸዋል።
የሲዳማ አማካዮች ቡድኑ ኳስ ከኋላ መስርቶ ሲወጣ እንዲሁም ወደ መከላከል ሲሸጋገር ከተከላካይ መስመሩ ብዙ ርቀው አይታዩም። ይህ ነጥብ ከኋላ መስመሩ ፊት ከሚኖረው የሁለትዮሽ ጥምረት በተጨማሪ ዋናውን የሲዳማን ፈጣሪ አማካይ ፍሬው ሰለሞንንም ይጨምራል። ሲዳማ በዚህ መልኩ ጨዋታውን ከቀረበ ከኳስ ውጪ የጅማን አማካዮች ለማፈን የተሻለ ዕድል ሊፈጥርለት ቢችልም የመስመር እና የፊት አጥቂዎቹ ከፍሬው በሚነሱ መካከለኛ እና ረዥም ኳሶች ላይ ተመስርተው ፈጣን ጥቃትን በመሰንዘር ላይ እንዲመሰረቱ ሊያደርጋቸው ይችላል። በእርግጥ እንደ ጅማ ሁሉ ሲዳማም ጥሩ ጊዜ ላይ ከሚገኙት ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ በዚህ ረገድ ጥሩ ብቃትን ለማግኘት ይጠብቃል።
ጅማ አባ ጅፋር ከወጣቱ ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ውጪ ቀሪ ስብስቡን ከጉዳት እና ቅጣት ውጪ ሆኖ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። በሲዳማ ቡና በኩልም ከጉዳት መልስ ልምምድ የጀመረው የግራ መስመር ተከላካዩ ሰለሞን ሀብቴ መግባት አጠራጣሪ ከመሆኑ ውጪ ሌሎች ተጫዋቾች ለጨዋታው ብቁ ናቸው።
ጨዋታው በለሚ ንጉሴ የመሀል ዳኝነት ሲከወን ሶርሳ ድጉማ እና ሻረው ጌታቸው ረዳቶች አሸብር ሰቦቃ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድበዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)
ተክለማርያም ሻንቆ
አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና
ቴዎድሮስ ታፈሰ – ሙሉዓለም መስፍን
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ፍሬው ሰለሞን – ብሩክ ሙሉጌታ
ይገዙ ቦጋለ
ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)
ዮሐንስ በዛብህ
ወንድማገኝ ማርቆስ – እያሱ ለገሰ – የአብስራ ሙሉጌታ – ተስፋዬ መላኩ
መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ
ዱላ ሙላቱ – በላይ አባይነህ – እዮብ ዓለማየሁ
መሐመድኑር ናስር