ከአምስተኛው ሳምንት በኋላ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ይመለሳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለበት የማጣሪያ ጨዋታዎች የተነሳ እስከ አምስተኛ ሳምንት ድረስ ሲደረግ የቆየው የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከነገ ጀምሮ በአዳማ ከተማ በስድስተኛ ሳምንት የጨዋታ መርሀግብር በይፋ ይመለሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው የሱፐር ስፖርት የቀጥታ ስርጭትም አብሮ እንደሚመለስ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አሳውቋል።
አክሲዮን ማህበሩ እንዳለው በቀጥታ ስርጭቱ ከሚተላለፉ መቶ ሰማኒያ ጨዋታዎች ውስጥ ስምንት ጨዋታዎች ሽፋን በማግኘታቸው በቀጣይ ከሚካሄዱ ጨዋታዎች ውስጥ መቶ ሰባ ሁለቱ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ይኖራቸዋል። በተጨማሪም የAi (Artificial intelligence) ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከስምምነቱ ውጭ ያሉ ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ አክሲዮን ማህበሩ ከሱፐር ስፖርት ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝም ጭምር አስታውቋል።