[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።
የተጫዋች አደራደር ቅርፅ 4-4-2 (ዳይመንድ)
ግብ ጠባቂ
መሳይ አያኖ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ከዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ የቋሚነት ዕድሉን አግኝቶ የነበረው የግብ ዘቡ መሳይ ቡድኑ ሰበታ ከተማ ላይ ድል እንዲቀዳጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ተጠባባቂ ወንበር ላይ በመክረሙ ትኩረቱን ያላጣው ተጫዋቹም በጥሩ ቅልጥፍናዎች የቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶችን ከግብነት ሲታደግ አስተውለናል። በጨዋታ ሳምንቱም እርሱን ጨምሮ ስምንት ግባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡ ግብ ጠባቂዎች ቢኖሩም ያዳናቸው ኳሶች ለግብነት የቀረቡ ስለነበር በምርጥ ቡድናችን ውስጥ አካተነዋል።
ተከላካዮች
ሱሌይማን ሀሚድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ያለፉትን ሰባት ጨዋታዎች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ ቡድኑን ሲያገለግል የነበረው ሱሌይማን በወልቂጤው ጨዋታ ዋናው ከነበረው የመከላከል ሀላፊነቱ በተጨማሪ ማጥቃቱም ላይ በሚገባ ሲሳተፍ ነበር። ተጫዋቹ በ85ኛው ደቂቃ ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ የግቡ ብረት የመለሰበትን ኳስ ጨምሮ ሌሎች ዕድሎችን ለአጋሮቹ በሦስተኛው የሜዳ ሲሶ እየተገኘ ሲፈጥር ነበር።
አንተነህ ጉግሳ (ወላይታ ድቻ)
ወላይታ ድቻ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን እንዲያገኝ የአንተነህ ጎል አስፈላጊ ነበር። የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ጎል ያስቆጠረው አንተነህ በመከላከል ሀላፊነቱ ተጋጣሚ የነበሩት የመከላከያ ተጫዋቾች በምቾት ጥቃት እንዳይፈፅሙ ከአጋሮቹ ጋር ሲለፋበት የነበረው መንገድ የሚደነቅ ነው። በዋናነትም መከላከያዎች ካደረጓቸው 12 ሙከራዎች ከሁለት ያልበለጡት ብቻ ዒላማቸውን የጠበቁ እንዲሆን እጅግ ጥሯል። ከዚህ ውጪም የቆሙ ኳሶችን በጥሩ ሁኔታ በመጠቀም የግብ ምንጭነት ሲሆን ተስተውሏል።
ወንድሜነህ ደረጄ (ኢትዮጵያ ቡና)
በዚህ ዓመት ከአሰላለፍ ርቆ የቆየው ወንድሜነህ ከአበበ ጋር የነበረውን ጥምረት ዳግም በጥሩ ሁኔታ የተገበረበት የጨዋታ ቀን አሳልፏል። በጉዳት ምክንያት ጨዋታውን ማጠናቀቅ ባይችልም በሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች ግን ለቡድኑ የመከላከል ሂደት የበኩሉን አድርጓል። በተለይም ከአዲስ አበባ አጥቂዎች ጋር በአንድ ለአንድ አጋጣሚዎች ያከሸፋቸው ኳሶች ወደ ግብ የመቀየር ዕድል የነበራቸው ነበሩ።
ሥዩም ተስፋዬ (ኢትዮጵያ ቡና)
አንጋፋው ተከላካይ ያካበተው ልምድ በኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር ውስጥ ያለውን ጥቅም ያሳየበትን የጨዋታ ቀን አስመልክቶናል። በቶሎ ወደ ኋላ ተመልሶ ዋና ኃላፊነቱ በነበረው የግራውን የቡድኑን ክፍል ከመከላከል ባለፈ በዚሁ መስመር የነበረው የቡድኑ የማጥቃት ሂደት የአዲስ አበባን የቀኝ መስመር እንዲያጠቃ ደጋግሞ ወደ ሳጥን በመቅረብ በሜዳው ቁመት ከሚጣመራቸው የቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ዕድሎችን ሲፈጥር ተስተውሏል።
አማካዮች
ጋቶች ፓኖም (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ቅዱስ ጊዮርጊስ በተደጋጋሚ በወልቂጤ ከተማ ላይ ይሰነዝር ከነበረው ፈጣን ጥቃት ጀርባ የግዙፉ አማካይ ሚና በግልፅ ይታይ ነበር። በተከላካይ መስመሩ ፊት በነበረው የጨዋታ ሚና የተጋጣሚን የማጥቃት ሂደት ከማቋረጥ ባለፈ ቡድኑ በቶሎ ወደ ማጥቃት እንዲሸጋገር ቅብብሎችን ይከውንበት የነበረበት መንገድ በቡድናችን እንድናካትተው አድርጎናል። ተጫዋቹ ከዚህ አልፎ ሳጥን ውስጥ ድረስ በመገኘት የግብ ዕድሎችን ሲፈጥርም ተመልክተናል።
ዳዊት ተፈራ (ሲዳማ ቡና)
በጨዋታ ሳምንቱ ድንቅ አሲስት ካሳዩን ተጫዋቾች ቀዳሚው ዳዊት ነው። በግራ እግሩ ኳስን እንዳሻው የሚያረገው ተጫዋቹ ቡድኑ ጅማን ሲረታ ሁለቱም ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል። አንደኛውን በፍፁም ቅጣት ምት ቢያስቆጥርም ለይገዙ ያቀበለው የመጨረሻ ኳስ ግን በግርምት እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን ነው። አራት እና አምስት ተጫዋቾችን ቀንሶ ካቀበለው ኳስ ውጪም በእንቅስቃሴ በድንቅ እይታዎቹ ሌሎች ኳሶችን ለአጋሮቹ ሲያመቻች አስተውለናል።
የአብስራ ተስፋዬ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍ ባለ የጨዋታ ፍጥነት በጀመረበት እና ግቦችን በጊዜ ባገኘበት ጨዋታ የአብስራ ተስፋዬ እጅግ ንቁ ሆኖ ታይቷል። ለቡድኑ ውጤታማነት ቁልፍ በነበረው ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ውስጥ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ ሂደቱ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን እንዲዘልቅ በማድረግ የተጨዋቹ እንቅስቃሴ ጉልህ እገዛ አድርጓል። የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር የግብ ዕድሉ እንዲፈጠር ያደረገበት መንገድ በሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች ለነበረው አስተዋፅዖ ቀላሉ ማሳያ ነው።
ዊሊያም ሰለሞን (ኢትዮጵያ ቡና)
ብቸኛው የዊሊያም የቀኝ እግር ጎል ቡና ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ አስችሏል። ያለ ተፈጥሯዊ ቦታው የቀኝ መስመር አጥቂ ሆኖ የተጫወተው ዊሊያም በጨዋታው አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም ግቡን ካገባ በኋላ በደንብ በማጥቃቱ ላይ ሲሳተፍ ነበር። በተለይ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ፍጥነቱን እና የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የቡና መሪነት ከፍ እንዲል ጥሯል። እንዳልነው ተጫዋቹ የቀኝ መስመር አጥቂ ሆኖ ቢጫወትም በምርጥ ቡድናችን ከአጥቂ ጀርባ ያለውን ቦታ ሰጥተነዋል።
አጥቂዎች
አብዱልከሪም ኒኪማ (ባህር ዳር ከተማ)
ባህር ዳር በሊጉ ከተጠቀማቸው ተጫዋቾች ሦስተኛው ብዙ ደቂቃዎችን የተጫወተው ኒኪማ (883) አዲስ በሆነበት የሀሰተኛ 9 ቁጥር ሚና ከጎል ጋር የተገናኘበትን ሳምንት አሳልፏል። ለወትሮ በአጥቂ አማካይ እና ከሳጥን ሳጥን የመሮጥ ሀላፊነት ተሰጥቶት ሲጫወት የምናውቀው ተጫዋቹ ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ከጠጣሮቹ የሀዋሳ ተካላካዮች ጋር ሲታገል ነበር። ዋነኛ አጥቂውን በጉዳት ላጣው ቡድንም ሁነኛ አማራጭ እንደሚሆን ይታለማል።
ኢስሜኤል ኦሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቶጓዊው ግዙፍ አጥቂ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣን ጥቃቶች መዳረሻ በመሆን ለማጥቃት ሂደቱ ስልነት አስፈላጊውን የፊት መስመር ኃላፊነት በመወጣት ቀጥሏል። ስምንተኛ የሊግ ጎሉን ባስቆጠረበት የወልቂጤው ጨዋታ ለፍፁም ቅጣት ምት መገኘት እና ለወልቂጤው ዮናስ በርታ ቀይ ካርድ መገኘት ምክንያት በመሆን ጊዮርጊስ በጊዜ ጨዋታውን እንዲጨርስ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወቱ ከ 10ኛው ሳምንት በኋላ የምርጥ ቡድናችን አጥቂ እንዲሆን አድርገናል።
አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ (ባህር ዳር ከተማ)
ከአህጉራዊ ግዳጅ መልስ በሊጉ የድሬዳዋ ቆይታ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የመሩት አሰልጣኝ አብርሀም ቡድናቸው ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል እንዲመለስ አድርገዋል። ሀዋሳን በረቱበት ጨዋታ ቡድኑ ከሰሞኑ ርቆት የቆየውን ከፍ ያለ ተነሳሽነት ተላብሶ ለተጋጣሚው የጨዋታ መንገድ ምላሽ እንዲሰጥ ማስቻላቸው እና ከእስካሁኑ ለየት ባለ የተጫዋቾች ሚና ምርጫ ወደ ሜዳ መግባታቸው ለውጤቱ የነበረው ድርሻ ከፍ ያለ በመሆኑ የሳምንቱ ተመራጭ አሰልጣኝ አድርገናቸዋል።
ተጠባባቂዎች
ቻርለስ ሉክዋጎ
ጀሚል ያዕቅብ
ፍሪምፖንግ ሜንሱ
አዲስ ህንፃ
ቻርለስ ሪባኑ
ፉአድ ፈረጃ
አሜ መሀመድ
ይገዙ ቦጋለ