“የሳላዲን ውሳኔ ተጫዋቹን እንድናከብረው የሚያደርግ እንጂ የሚያስወቅሰው አይደለም” አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

ሳላዲን ሰኢድ ከብሄራዊ ቡድኑ ውጪ መሆኑ ከተሰማ በኋላ በሚሰጡት አስተያየቶች ደስተኛ እንዳልሆኑ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሳላዲን በቡድናቸው መካተት ለአልጄርያው ጨዋታ የሚጠቅም ቢሆንም በአካል እና አእምሮ ብቁ ባለመሆኑ እንዳልተሳካ ገልፀዋል፡፡

“ሳላዲንን የመረጥነው አንደኛ ተጋጣሚያችን አልጄርያን በደንብ ስለሚያውቅ ሁለተኛ ተጨዋቹ እዚህ አዲስ አበባ እንደመገኘቱ ምንም ወጪ ሳናወጣ ለሙከራ ጠርተነው አቋሙ ጥሩ ከሆነ ወደ ዋናው የቡድን ስብስብ ለማካተት ነበር፡፡ ከምንም በላይ ግን ተጫዋቹ ያለው የብሄራዊ ቡድን ልምድ ይጠቅመን ነበር ሆኖም አልተሳካም፡፡ ” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ አክለውም የሳላዲን ውሳኔ ተጫዋቹን እንዲያከብሩት እንዳደረጋቸው አብራርተዋል፡፡ “አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ሳላዲን በቂም በቀል ምክንያት ነው አልጫወትም ያለው ሲባል እሰማለው፡፡ ለምን እሱ ያላለውን ነገር እናወራለን? እነሱ እንዳሉት ቢሆን ኖሮ ለምን በግልፅ እንነጋገራለን? ለምን የቡድኑ ልምምድ ላይ እየመጣ ተጨዋቾቹን ያበረታታል? ለምን ከኛ ጋር ተሰብስቦ የቡድኑን መንፈስ ለማሳደግ ምሳ አብሮን ይበላል? ለብሄራዊ ቡድን የሚጫወተው እኮ ሀገሩን ለመወከል እና የሀገሩ ብሄራዊ ቡድን ጥሩ ውጤት እዲያመጣ ነው፡፡ እኔ እንደውም አከብረዋለው፡፡ ሳላዲን ያለው እኮ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ 80 ሚልየን ህዝብን ለመወከል በአካልም ሆነ በአእምሮ ጉዳዮች ብቁ ስላልሆነ ለሌሎች ተጨዋቾች እድል እንዲሰጥ ነው የነገረኝ፡፡ ይህ ተጨዋቹን እንድናከብረው የሚያደርግ ነገር ነው እንጂ የሚያስወቅስ አይመስለኝም፡፡ ” ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *