” በአልጀርሱ ጨዋታ ስህተቶች ለመቀነስ ጥረት እናደርጋለን” አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የፊታችን አርብ ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ቡድኑ ዛሬ ወደ አልጄሪያ ያመራል፡፡ ዛሬ 11:00 ላይ በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስለብሄራዊ ቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ እኛም አጠር አድርገን እንዲህ አሰናድተነዋል፡፡

ስለ ጉዳት “ከመረጥናቸው 24 ተጨዋቾች ሶስቱ በጉዳት (ታፈሰ ተስፋዬ ፣ ሙሉአለም ጥላሁን እና ስዩም ተስፋዬ) እንዲሁም ሳላዲን ሰኢድን በግሉ ባለው የአእምሮ እና የአካል ዝግጁነት ብቁ አለመሆን ምክንያት በማጣታችን ስብስባችንን ከባድ አድርጎት ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ማጣት ቀላል አይደለም፡፡ ”

ስለ ቡድኑ ዝግጅት “በአንድ ሳምንት ውስጥ በ13 ተጨዋቾች ጀምረን በ17 ተጨዋቾች ልምምዳችንን አድርገናል፡፡ ነገር ግን ዝግጅታችን በወዳጅነት ጨዋታ አለመታገዙ ሙሉ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ፌደሬሽኑ የወዳጅነት ጨዋታ ለማዘጋጀት ጥረት ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ነገር ግን ወደ ውድድር ለመግባት ዝግጅት ላይ ስለሆንን ይህንን እንደ ምክንያት መጥቀስ አንፈልግም፡፡ ”

ጉዞ “የጉዞው ነገር እጅግ አድካሚ እንደሚሆን እናስባለን፡፡ የሁለት ቀን መንገድ ነው፡፡ ረጅም የጉዞ ፕሮግራም እንደመሆኑ የጉዞ መዘግየት እና ተያያዥ ምክንያቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ እኛም ቀደም ብለን ጉዞዋችንን ጨዋታው ከሚደረግበት ቀን አራት ቀናት አስቀድመን ወደ ስፍራው ለመሄድ ወስነናል፡፡ ከቡድኑ ተጨዋቾች ጉዞውን ከባድ የሚያደርገው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ለተመረጡት ተጨዋቾች ነው፡፡ ለክለባቸው በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ወደ ኮንጎ ማምራታቸውን ተከትሎ አዲስ አበባ ላይ ምንም ልምምድ ሳያደርጉ እዛው አሮፕላን ማረፊያ ቡድኑን ተቀላቅለው ረጅም ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ”

ስለ ጨዋታው ” በአራት ቀናት ውስጥ ሁለት ጨዋታ እንደማድረጋችን ሀይላችንን ቆጥበን ቡድኑን ሊጠቅሙ ይችላሉ የምንላቸውን ነገሮች ለመጠቀም ጥረት እናደርጋለን፡፡ በሰው ሰራሽ ሜዳ ጨዋታውን እንደማድረጋችን እና የምንጫወትበት ሜዳ ጠባብ እንደመሆኑ ብሎም የአየር ሁኔታው ብርዳማ እና ንፋሳማ እንደመሆኑ መሬት ላይ ያተኮረ ጨዋታን ለመጫወት እንሞክራለን፡፡ ”

ስለ ቡድናችን የአልጀርስ እቅድ “ከምንም በላይ ዋንኛ እቅዳችን በመጀመሪያው ጨዋታ ስህተቶችን መቀነስ እንዳለብን ስለምናምን ስህተቶችን ለመቀነስ ጥረቶችን እናደርጋለን፡፡ በመጀመሪያው እና በመልሱ ጨዋታ መካከል ያለው የቀናት ልዩነት ጥቂት ስለሆነ ከሜዳ ውጭ በሚደረገው ጨዋታ ላይ ሞራላችንን የሚነካ ውጤት እንዳይፈጠር ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ ”

ስለ ተጋጣሚያቸው “ተጋጣሚያችንን አንፈራም፡፡ ነገር ግን እንደ ማንኛውም ተጋጣሚ እናከብራቸዋለን፡፡ ቡድኑ በወዳጅነት ጨዋታ ላይ ያደረገው እንቅስቃሴ ጨምሮ ሌሎች ምስሎችን ለማየት እና ቡድኑን ለማጥናት ሞክለናል፡፡ ከዚም በላይ የአንዳንድ ተጨዋቾችን ወቅታዊ የግል ብቃቶችን በማየት ስለቡድኑ መረጃ ሰብስበናል፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *