[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር አሸናፊ የሆነው ንግድ ባንክ ተጫዋቾቹን እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱን እውቅና ሰጥቷል።
እንደ ክለብ 1975 ላይ የተመሰረተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነሐሴ 24 2003 ከሴንትራል የጤና ኮሌጅ ሙሉ ስብስቡን ገዝቶ የሴቶች ቡድን እንዳቋቋመ ይታወቃል። ከምስረታው ጀምሮ በአንድ አሠልጣኝ (ብርሃኑ ግዛው) እየተመራ የሚገኘው ክለቡም በተጠናቀቀው የ2013 የውድድር ዘመን የሊጉን ውድድር በአሸናፊነት አጠናቆ እንደነበር አይዘነጋም። ውድድሩንም በአሸናፊነት ማገባደዱን ተከትሎ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከናወነው የሴቶች የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የምስራቅ አፍሪካ የማጣሪያ ውድድር አከናውኖ ሁለተኛ ወጥቶ ነበር።
ታዲያ ለዚህ ስኬቱ የክለቡ አመራሮች ዘግይተው ቢሆንም የቡድን አባላቶቹን በትናንትናው ዕለት እውቅና ሰጥተዋል። አመሻሽ ላይ ልደታ አካባቢ በሚገኘው የባንኩ መስሪያ ቤት በተከናወነው መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ፣ የስፖርት ማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ዓሊ መሐመድ እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተው ሽልማቱን አበርክተዋል። በዚህም በሦስት ደረጃዎች ክለባቸው የሊጉን ዋንጫ እንዲያገኝ ያደረጉ ተጫዋቾች ከፍተኛው የ30 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም በኬኒያ በተደረገው የዞኑ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር ላይ ሁለተኛ ስለወጡ ደግሞ ተጨማሪ የ20 ሺ ብር በአጠቃላይ የ50 ሺ ብር ሽልማት በከፍተኛ ደረጃ ተሰጥቶ ተጫዋቾቹም እንደየተጫወቱበት ደቂቃ ሽልማታቸውን ተረክበዋል። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም በተመሳሳይ 50 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።
ከዚህ በተጨማሪ የ2013 የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ተብላ የተመረጠችው ረሂማ ዘርጋው፣ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆና ያጠናቀቀችው ሎዛ አበራ እና ኮከብ አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተጨማሪ 10 ሺ ብር ሲበረከትላቸው ረሂማ ግን ክለቡ በሚተዳደርበት ደንብ መሠረት በአሁኑ ሰዓት በስብስቡ ባለመኖሯ የተዘጋጀው ሽልማት እንደማይሰጣት ተገልጿል።