በምሽቱ ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች እጅግ ማራኪ ከሆነ እንቅስቃሴ ጋር ፋሲል ከነማን 2-0 ማሸነፍ ችለዋል።
በምሽቱ ተጠባቂ መርሐግብር ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ከስድስተኛ ሣምንት ጨዋታቸው በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ዐፄዎቹ ሀምበርቾን 3-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ቃልኪዳን ዘላለምን አሳርፈው በሱራፌል ዳኛቸው ሲተኩ የጦና ንቦች በአንጻሩ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 1-1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ዮናታን ኤልያስን አሳርፈው ዘላለም አባተን በማስገባት ለጨዋታው ቀርበዋል።
12፡00 ሲል በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የወላይታ ድቻ ፍጹም የበላይነት የታየበት ነበር። ገና በ 3ኛው ደቂቃ ቢኒያም ፍቅሩ በሳጥኑ የግራ ክፍል መናፍ አወልን አታልሎ በማለፍ በሞከረው እና ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ በእግሩ በመለሰው ኳስ የዐፄዎቹን ሳጥን መፈተን የጀመሩት የጦና ንቦች ተጭነው በመጫወት እና ኳስ ሲነጠቁ ደግሞ ጥቅጥቅ ብለው በመከላከል ለተመልካች ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል።
ሱራፌል ዳኛቸው ካደረጋቸው ፈታኝ ያልሆኑ ሁለት ሙከራዎች ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ፋሲሎች 34ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ነበር። ጸጋዬ ብርሃኑ ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ መረቡ ላይ ሊያርፍ ሲል ግቡን ለቆ ወጥቶ የነበረው ግብ ጠባቂው ሳማኬ እንደምንም አስወጥቶታል።
እጅግ በተጋጋለ የጨዋታ ስሜት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ድቻዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ቢኒያም ፍቅሬ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኢዮብ ማቲያስን አታልሎ በማለፍ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ሳማኬ ሚኬል የእጅ ንክኪ አቅጣጫ ቀይሮ ግብ ሆኗል።
ከወትሮው በተለየ ከጠንካራ እንቅስቃሴያቸው እጅግ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ዐፄዎቹ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተደራጅተው ለመግባት ሲቸገሩ ወላይታ ድቻዎች በአንጻሩ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ 45ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን አጠናክረዋል። አበባየሁ ሀጂሶ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሳማኬ ሚኬል ደካማ በሆነ አጠባበቅ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው ዘላለም አባተ በቀላሉ አስቆጥሮት አጋማሹ በወላይታ ድቻ 2-0 መሪነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።
ከዕረፍት መልስ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቃልኪዳን ዘላለምን እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማነቃቃት ጥረት ሲያደርጉ የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ተጫዋቾች በአንጻሩ ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በሚያገኙት ኳስ ግን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል። በዚህ እንቅስቃሴም በተለይም 53ኛው እና 55ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ያለቀላቸው ኳሶች በሁለቱም የሳጥኑ ክፍሎች ላይ አግኝተው አጥቂው ቢኒያም ፍቅሬ በደካማ ውሳኔ አባክኗቸዋል።
ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በተደረገባቸው የመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች ድቻዎች በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ፋሲሎች በአንጻሩ ባልተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታው በወላይታ ድቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የዐፄዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ እንዳለቀ እና ተጋጣሚያቸው ድሉ እንደሚገባቸው በመናገር ባልተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ምክንያት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር መቸገራቸውን ገልጸው ተጋጣሚያቸውን እንደጠበቁት ስለማግኘታቸው በመጠቆም ያሰቡትን ጨዋታ ስላለማግኘታቸው አልሸሸጉም። በጨዋታው ድል የቀናቸው የወላይታ ድቻው አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው ያሰቡትን አጨዋዎት በመጀመሪያው አጋማሽ ካሳኩ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለማስጠበቅ ስለመጫወታቸው ጠቁመው ልምምድ ላይ የሰሩትን ታክቲክ ሜዳ ላይ ማግኘታቸውን በመናገር የሚባክኑ ኳሶች በአጥቂዎቻቸው ብስለት ማጣት እንደሆነ በማመን ወደፊት ከስህተታቸው ተምረው የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ሀሳባቸውን ገልጸዋል።