ሪፖርት | ለከርሞ በሊጉ መቆየታቸውን ያረጋገጡት ሠራተኞቹ ዓመቱን በድል አገባደዋል

ከነገው የሊጉ መዝጊያ ጨዋታ አስቀድሞ በተካሄደው የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምት ተስቶበት ወልቂጤዎችን አሸናፊ በማድረግ አብቅቷል።

የሊጉን የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው አስቀድሞ ሽንፈት አስተናግደው የተመለሱት አዳማ ከተማዎች ከስብስባቸው የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሬዲዋን ሸሪፍ፣ ነቢል ኑሪ እና ሱራፌል ዐወል አሳርፈው ታዬ ጋሻው፣ አቤነዘር ሲሳይ እና ቦና አሊ ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ሀምበሪቾን በመርታት ለከርሞ በሊጉ መሰንበታቸውን ያወቁት ወልቂጤዎች በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ዳንኤል ደምሴ፣ ጌቱ ሃይለማርያም ተመስገን በጅሮንድ አስቀምጠው ዮሴፍ ታምሬ፣ አልሀሺም ግራኝ እና ፉአድ አብደላ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

የዓምናው የሊጉ ምስጉን ዳኛ የነበሩት ፌደራል ዳኛ ቢንያም ወርቅአገኘው አስራ ሦስተኛ ጨዋታቸውን በመሩበት በዚህ ጨዋታ ገና በጨዋታው ጅማሬ ቢንያም አይተን ከሳጥን ውጭ ባደረገው ጠንከራ ባላለ ምቱ ግብጠባቂው ፋሪስ አለው ከያዘበት ሙከራ በኋላ ዳግም ቢንያም በ4ኛው ደቂቃ ቦና አሊ በጥሩ መንገድ ያሻገረለትን በተረጋጋ ሁኔታ ኳሱን ባልተለመደ እግሩ ደገፍ አድርጎ የመታውን የግቡ ቋሙሚ የመለሰው አዳማ ከተማዎች በፍጥነት ጨዋታውን ለመቆጣጠር የወልቂጤን የግብ ክልል የጎበኙበት ነበር።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ሠራተኞቹ አዳማ ከተማን የሚፈትን አደጋዎችን መሰንዘር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ማስመልከት አልቻሉም። በአንፃሩ አዳማዎች ፈጣኖቹን አጥቂዎቻቸውን በመጠቀም በተደጋጋሚ የወልቂጤን የሜዳ ክፍል መድረስ ችለዋል። በዚህም ሂደት በ19ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን መድህን ተክሉ በራሱ ላይ ጎል ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ግብጠባቂው ፋሪስ አድኖታል።

የጨዋታውን መልክ ይቀይራል ተብሎ የሚጠበቅ ፍፁም ቅጣት ምት በ21ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ጳውሎስ ቢንያም አይተን ላይ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅመሀል በማለት የዕለቱ ዳኛ የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት በአዳማ በኩል ቦና አሊ ቢመታውም ግብጠባቂው ፋሪስ አለው በግሩም ሁኔታ ጎል እንዳይሆን አድርጎታል። ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች ከአስር ደቂቃ በኋላ ሌላ ጎል የሚሆን አጋጣሚ ወደ ሳጥን የተላከውን ጀሚል ያዕቆብ ግብጠባቂውን ፈሪስ አልፎ በመቀስ ምት ወደ ጎል ቢልከውም የግቡ ቋሚ ጎል እንዳይሆን ከልክሏቸዋል።

የቡድን ውህደት ችግር የሚታይባቸው እና ወደ ሳጥን ሲጠጉ ዕብዛም ጥራት ያለው ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ውስንነት የነበራቸው ሠራተኞቹ ጨዋታውን መቆጣጠር የሚችሉበትን ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ነበር። 33ኛው ደቂቃ ፉአድ አብደላ ላይ ታዬ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምትን ጋዲሳ መብራቴ በደካማ ምት ኳሱን ወደ ውጭ ሰዶታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ሙሴ ኪሮስ እና ነቢል ኑሪን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ኃይላቸውን በማጠናከር ያደረጉት ጥረት በተወሰነ መልኩ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ ቢያመጣም ይሄን ያህል ስኬታማ አልነበረም። የጨዋታው የኃይል ሚዛን የተወሰደባቸው ወልቂጤዎች በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ የሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ካልሆነ በቀር ተጠቃሽ ዕድሎች አሁንም መፍጠር አልቻሉም። በዚህ ሄደት ደግሞ 61ኛው ደቂቃ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በቋሚ አስራ አንድ ውስጥ የገባው አልሀሺም ግራኝ ነቢል ኑሪ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ በቀይ ካር ከሜዳ መውጣቱ የወልቂጤዎችን ፈተና በቀሪ ደቂቃዎች እንዳያከብደው ተሰግቶ ነበር።

አዳማ ከተማ በጨዋታው እንደነበራቸው የበላይነት እና የቁጥር ብልጫ በቀሪ ደቂቃዎች ጎል የማስቆጠር ዕድል ይኖራቸዋል ቢባልም የሆነው በተቃራኒው ነው። 72ኛው ደቂቃ ተመስገን በጅሮንድ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ አዳነ በላይነህ ኳሱ አየር ላይ እንዳለ በቀጥታ በጠንካራ ምት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከወትሮው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የነበራቸውን ጥንካሬ ያጡት አዳማ ከተማዎች በክፍት ሜዳ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከሞመከር ይልቅ በረጃጅም ኳሶች የሚያደረጓቸው ጥረቶች ደካማዎች ነበሩ። በአንፃሩ በጨዋታውን የመጨረሻ ደቂቃ ሳይቸገሩ ጨዋታውን በተገቢው መንገድ ማስኬድ የቻሉት ሠራተኞቹ ውጤቱን ይዘው ሊወጡ ችለዋል።

ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት አሠልጣኝ ሙልጌታ ምህረት ብዙም የተለወጠ ነገር የለም በነፃነት መጫወታቸው ውጤቱን እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ገልፀው በቡድኑ የነበራቸውን ቆይታ ማጠናቃቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል። ተሸናፊው አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ፈታኝ ዓመት እንዳሳለፉ እና ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች ለቡድኑ ውጤት መጥፋት ከክለቡ የክፍያ አለመከፈል ጋር ተያይዞ እንደሆነ ተናግረው ቡድናቸው የተሻለ አፈፃፀም የኖረው የጨዋታ መንገዳቸውን አለመቀየራቸው እንደሆነ እና ዓመቱን በተሻለ መፈፀማቸውን ተናግረዋል።