[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ሲዳማ ቡና እና ወልቂጤ ከተማን ያገናኘው የ13ኛ ሳምንት የማሳረጊያ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።
ጅማ አባጅፋርን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ረተው ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት ሲዳማ ቡናዎች ሦስት ነጥብ ካገኙበት ጨዋታ ጊት ጋትኩትን በተስፋዬ በቀለ ብቻ ለውጠው ወደ ሜዳ ሲገቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የአራት ለምንም ሽንፈት ገጥሟቸው የነበረው ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ አህመድ ሁሴን እና ዮናስ በርታን አሳርፈው ተስፋዬ ነጋሽ እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን ወደ አሰላለፍ አምጥተው ጨዋታውን ቀርበዋል። ከቀናት በፊት አሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸውን ተክተው የመጡት አሠልጣኝ ተመስገን ዳና የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ለማድረግ በቦታው ተሰይመዋል።
የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች ፈጠን ያለ እንቅስቃሴ በማድረግ ቀዳሚ ለመሆን ጥረዋል። እስከ 12ኛው ደቂቃም አራት ጥቃቶችን ሲዳማዎች ላይ ሰንዝረው ተመልሰዋል። በተለይ ረመዳን እና ጌታነህ አከታትለው የሞከሯቸው ሙከራዎች አስደንጋጭ ነበሩ። ገና በጊዜ ጫና የበዛባቸው ሲዳማዎች በሩብ ሰዓት በቴዎድሮስ ታፈሠ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ኳስ ወደግብ ልከው ወጥቶባቸዋል።
ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ተደራጅተው በመጫወት ለሲዳማ አጨዋወት አልመች ያሉት ወልቂጤዎች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተነሳሽነት ታይቶባቸዋል። በ24ኛው ደቂቃም እጅግ ሳቢ በሆነ የቡድን ስራ በኃይሉ ተሻገር ከጫላ ተሺታ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ግብ አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም የተሳሳተ የረዳት ዳኛ ውሳኔ ተከስቶ ግቡ ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሯል። ያልጠበቁት ፈተና የገጠማቸው የሚመስሉት ሲዳማዎች ግቡ እንደተሻረ ፈጣን ጥቃት በሰከንዶች ልዩነት አድርገው ነበር። ነገርግን የመጨረሻው ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ የደረሰው ዳዊት ተፈራ ኳሱን ከዒላማ ውጪ አጉኖታል።
በ43ኛው ደቂቃ ሲዳማ ወርቃማ ዕድል አግኝቶ ነበር። በዚህም ፍሬው ሰለሞን ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘ የቅጣት ምት ሲሻማ የግብ ዘቡ ሰዒድ ሃብታሙ የወረደ የጊዜ አጠባበቅ ተከትሎ ግቡን ለቆ ሲወጣ ያኩቡ መሐመድ ደርሶት በግንባሩ ወደ ግብ ቢመታውም ውሀብ አዳምስ ኳስ የግብ መስመሩን ከማለፉ በፊት እንደምንም አውጥቶት ከግብነት አግዶታል። አጋማሹ ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢያስመለክትም ያለ ግብ ተጠናቋል።
ሁለት ተጫዋቾችን በመቀየር ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ሲዳማዎች በ54ኛው ደቂቃ በቁጥር በርከት ብለው በማጥቃት ሀብታሙ ሙከራ አድርጎ ነበር። ለዚህ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡት ወልቂጤዎች በደቂቃ ልዩነት ሁለት ጊዜ ሰዒድን ፈትነዋል። በቅድሚያ ጫላ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ መቶት ለጥቂት ሲወጣበት ጌታነህ ደግሞ ከሳጥን ውጪ አግኝቶ በቀጥታ የመታውን ኳስ ተክለማርያም አድኖበታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያደርጉት የነበረውን ፍጥነት የታከለበት አጨዋወት ጋብ ያደረጉት ወልቂጤዎች ወረድ ያለ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተከትሎ ሲዳማዎች እያደጉ መተው ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ሲዳማ የሰላ ጥቃት መፈፀም ተስኖት ታይቷል። ሲዳማ ብቻ ሳይሆን ወልቂጤም ከድካም የመጣ መዛል ያጋጠማቸው በሚመስል መልኩ እጅግ ተዳክመው ጨዋታውን ለመፈፀም ተገደዋል። ሁለት መልክ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም ያለ ግብ ፍፃሜውን አግኝቷል።
ወደጨዋታው ሲገቡ ይዘውት የገቡትን አንድ ነጥብ ይዘው ከሜዳ የወጡት ሲዳማ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ በቅደም ትከተል 19 እና 17 ነጥቦችን በመያዝ አምስተኛ እንዲሁም አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።