ሪፖርት | የሊጉን ተሰናባች ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ በሻሸመኔ አሸናፊነት ተቋጭቷል

ባለፈው ሳምንት ወደ ከፍተኛ ሊግ የተሸኙ ክለቦችን ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ በመጀመሪያ አጋማሽ ጎሎች ሀምበሪቾን 3ለ1 በመርታት ዓመቱን በሽንፈት ጀምሮ በድል ከሊጉ ተሰናብቷል።

ሻሸመኔ ከተማ መውረዱን ካረጋገጠበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ጨዋታ የስምንት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርግ በተመሳሳይ በወልቂጤ ከተማ ተረተው የነበሩት ሀምበሪቾዎች ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ምንታምር መለሠ ፣ ታዬ ተሰማ እና በፍቃዱ አስረሳኸኝ አርፈው ፓሉማ ፓጁም ምናሴ ብራቱ እና አብዱልከሪም ኑዱጉዋ ተተክተው ገብተዋል።

ሁለቱን የሊጉ ተሰናባች ክለቦችን ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ቀዝቀዝ ያለ መልክን ተላብሶ ወረድ ባለ አቀራረብ ጅምሩን ቢያደርግም በሂደት ግን የሻሸመኔ ከተማ ብልጫን ያየንበት ሆኗል። 2ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን አሰፋ ከቅጣት ባደረጋት እና ግብ ጠባቂው ኬኒ ሰይድ ባመከናት ሙከራ ቀዳሚ ጥቃት አድራሾች ሀምበሪቾዎች ቢሆኑም ጨዋታው አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሲሻገር ሻሸመኔ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን በመያዝ 18ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል ። ስንታየሁ መንግስቱ በጥሩ ዕይታ የሰጠውን ኳስ ሳጥን ውስጥ የተገኘው ሱራፌል ሙሉወርቅ በድንቅ አጨራረስ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ደካማውን የሀምበሪቾ ተከላካዮች በተደጋጋሚ ጫና ማሳደርን አጠናክረው የቀጠሉት ሻሸመኔ ከተማዎች 37ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።


ከመሐል መነሻዋን ያደረገች ኳስን ከቀኝ የሜዳው ክፍል አብዱልቃድር ናስር የተቀበለው ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሳልፍ ስንታየሁ መንግስቱ ወደ ግብነት የለወጠው ተጫዋች ነው። ጨዋታውን መቆጣጠር እየከበዳቸው የመጡት እና በሽግግር ለመጫወት ጥረት የሚያደርጉት የአሰልጣኝ ብሩክ ሲሳዩ ሀምበሪቾ 44ኛ ደቂቃ ሦስተኛ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል። ተከላካዩ አዲስዓለም ተስፋዬ የተሳሳተውን ኳስ ያገኘው አብዱልቃድር ናስር ለአጥቂው ስንታየሁ ሲያቀብለው ተጫዋቹ የግል አቅሙን ተጠቅሞ ተጫዋቾችን በማለፍ ጭምር ለራሱ እና ሁለተኛ ለቡድኑ ሦሰተኛ ጎል በማድረግ አጋማሹ በ3ለ0 ውጤት ተጋምሷል።


ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ተመጣጣኝ ፉክክርን መመልከት ብንችልም በማጥቃቱ ረገድ ግን ውስንነቶች ታይተዋል። አጋማሹ እንደተጀመረ ሻሸመኔ ከተማ በስንታየሁ መንግስቱ ያለቀለትን አጋጣሚ በመፍጠር ቀዳሚ መሆን ሲችሉ 50ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሀምበሪቾዎች አብዱልከሪም ኑዱጉዋ ከቀኝ ሰብሮ ገብቶ ያቀበለውን ምናሴ በራቱ በሚያስቆጭ መልኩ ስቶታል።


እምብዛም ከሚደረጉ የተዳከሙ እንቅስቃሴዎች በስተቀር በሙከራዎች መድመቅ ያልቻለው ቀሪዎቹ ደቂቃዎች አልፎ አልፎ በመሰመር መንቀሳቀስ የቻሉት ሀምበሪቾዎች 79ኛው ደቂቃ ከቀኝ በሀይሉ ተሻገር ሳጥን ውስጥ ሆኖ ከግብ ጠባቂው ኬኒ ሰይዲ ጋር ተገናኝቶ ያደረጋት መልካም ዕድልን ሳይጠቀምባት ቀርቷል። 85ኛው ደቂቃ ሻሸመኔ ከተማዎች በስንታየሁ መንግስቱ ተጨማሪ ግብ የሚሆን ኳስን አምክነዋል።

የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች በስልነት ሲያጠቁ የታዩት ሀምበሪቾዎች ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ 90+5 ላይ የሻሸመኔው ተከላካይ ኤቢሳ ከድር በሳጥን ውስጥ በእጆ ኳስን በመንካቱ በዕለቱ አንደኛ ረዳት ዳኛ በሆነው ዘሪሁን ኪዳኔ ጥቆማ ብርሀኑ አሻሞ ማስተዛዘኛ ጎልን አስቆጥሮ ጨዋታው በሻሸመኔ ከተማ 3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።


የሀምበሪቾው አሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ በጨዋታው የጠበቁት እንደገጠማቸው በመግለፅ ያለ ቅያሪ 11 ተጫዋቾችን ብቻ ይዘው እንደተጫወቱ እና እናሸንፋለን የሚል ሀሳብን እንዳልነበራቸው በመናገር ውጤት ጠፋ በማለት ደጋፊው ከክለቡ መራቅ እንደሌለበት ክለቡም በቀጣይ ተምሮ በደንብ መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመው ከጎኔ ለነበሩ ተጫዋቾች እና ጓደኞቼ አመሰግናለሁ እግዚአብሔር ይመስገን በማለት ተናግሯል።

የሻሸመኔ አቻቸው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የገጠሙት ተቀያሪ ተጫዋቾች የሌሉት ክለብን በመሆኑ በሊጉ ማዘናቸውን ጠቁመው እንደ ጨወታ ማሸነፋቸው ጥሩ ቢሆንም ከታች የሚመጡ አዳዲስ ክለቦች ከእኛ መማር አለባቸው ከውድድሩ በላይ ራሳቸውን በፋይናንስ ማዘጋጀት አለባቸው እንደ ውጤት አሸንፍን ማለት ይከብደኛል በዚህ አጋጣሚ ተጫዋቾችን እየለመ ያጫውት የነበረውት የሀምበሪቾን አሰልጣኝ በማድነቅ ንግግራቸውን አጠናቀዋል።