“ህዝባችንን ወደ ዋና ከተማ ሳንመልስ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት መመኘት የማይጣጣሙ ነገሮች ናቸው” መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ

የሊጉ አክስዮን ማህበር ፕሬዝደንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የ2016 የውድድር ዘመን መዝጊያ መርሐ ግብር አስመልክቶ ከሱፐር ስፖርት ጋር በተለያዮ ጉዳዮች ዙርያ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ያነሱበትን አጭር ቆይታ አድርገዋል።

መቶ አለቃ በመጀመርያ የዘንድሮ የውድድር ዓመት በምን መልኩ እንደተጠናቀቀ ሲናገሩ “የ2017 የውድድር ዘመን ብዙ ነገር ተስፋ ያደረግንበት ተስፋችንን ግን ተግባራዊ ያልሆነበት የፈተና ዘመን ነበር። በመጨረሻ ግን በመልካም ሁኔታ የጨረስንበት ፈታኝ እና ድብልቅልቅ ያለ ዘመን ነበር።” በማለት ከገለፁ በኋላ ከሜዳ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን ፈተና እንዲህ ብለው ገልፀዋል። “ እንደሚታወቀው አዲስ አበባ የኢትዮጵያ እግርኳስ ማዕከል ነች ፤ የሊጉ ውድድር ወደ አዲስ አበባ አለመመለሳችን እጅግ እጅግ በጣም ቅሬታ አለብን። የእኛ ቅሬታ ብቻ ሳይሆን ሱፐር ስፖርት ባዶ ሜዳ በየገጠሩ እያሳያሳያቹሁ ለራሳችን ትርፍ አላገኘንበት፣ ለእናተም ቢሆን የሚጠቅም አይደለም የሚል ጭቅጭቅ እና ንትርክ ውስጥ የገባንበት ወቅት ነበር። አሁን ምን አልባት እንደተባለው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ተነስታለች የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ሁሉም ከተሞች የእግርኳስ ተመልካች እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ከዚሁ ከነገው ጀምሮ መለማመድ አለባቸው” ያሉት መቶ አለቃ በቀጣይ ዓመት አዲስ አበባ የሊጉን ውድድር ለማዘጋጀት ተስፋ አለ ይሆን ? ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ “ እንግዲህ እኔ በጣም ትልቅ ተስፋ አለኝ ህዝባችንን ወደ ዋና ከተማ ሳንመልስ የአፍሪካን ዋንጫን ለማዘጋጀት መመኘት የማይጣጣሙ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ በከተሞቻችን ላይ እግርኳስ ጨዋታን በስፋት ማካሄድ ይኖርብናል። ከተሞቻችን ሆቴሎቻችን ፣ ስታዲዮሞቻችን፣ ፖሊሶቻችን ጭምር በዛ ያለውን ህዝብ እንዴት ማስተናገድ መቻል እንዳለባቸው ከነገ ጀምሮ መለማመድ ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

በመጨረሻም የሊጉ ውድድር በቀጣይ ዓመት መቼ እንደሚጀመር ሲጠየቁ ገና ያልተወሰነ ቢሆንም ነሐሴ ወር ለመጀመር ተስፋ እንደሚያደርጉ እና በቅርቡ ለክለቦች እንደሚያሳውቁ ጠቁመው አልፈዋል።