ዋልያዎቹ ዛሬ ምሽት ወደ አልጄርያ ያመራሉ

የኢትዮጰያ ብሄራዊ ቡድን አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከአልጄርያ ጋር ለሚያደረገው ጨዋታ ዛሬ ምሽት ወደ አሌጄርያ ጉዞውን ይጀምራል፡፡ ብሄራዊ ቡድናችን ያለፉትን 2 ሳምንታት ተሰባስቦ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በዛሬው እለት እረፍት በማድረግ ልምምድ ሳይሰራ ቀርቷል፡፡

በብሄራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ከሚገኙት 17 ተጫዋቾች እና ከኮንጎ ተነስተው ዛሬ ምሽት 2፡00 አዲስ አበባ ከሚገቡት 4 የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በድምሩ ከ21 ተጫዋቾች መካከል ምንም ተጫዋች እንደማይቀነስና ሁሉም ወደ አልጄርያ እንደሚያቀኑ ከብሄራዊ ቡድኑ አካባቢ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

21 ተጫዋቾችን ፣ የአሰልጣኝ እና የህክምና ቡድን እዲሁም የቡድን መሪውን የያዘ አውሮፕላን 04፡45 ላይ የአልጄርያ በረራውን ሲጀምር ከሶት ሰአት በረራ በኋላ ግብጽ ካይሮ ይደርሳል፡፡ አዳሩን በካይሮ ካደረገ በኋላም ነገ ጠዋት ወደ አልጄርያ ይጓዛል፡፡ በምድብ 10 ሶስተኛ ጨዋታ አልጄርያ እና ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጨዋታ በመጪው አርብ የሚካሄድ ሲሆን በ4ኛው ጨዋታ በድጋሚ ሁለቱ ቡድኖች ማክሰኞ አዲስ አበባ ላይ ይጫወታሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በብሄራዊ ቡኑ ጉዞ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ 11፡00 ላይ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ይካሄዳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *