የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር የመልስ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተደርገው 16ቱ አላፊ ክለቦች ታውቀዋል፡፡ በእሁድ ጨዋታዎች የሊቢያው አል አሃሊ ትሪፖሊ እና የአልጄሪያው መውሊዲያ ቤጃ ታጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ሳይጠበቁ ወደ ሁለተኛው ዙር አልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ተወካዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2015 የቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ ቲፒ ማዜምቤ ከውድድሩ ሲሰናበት የአልጄሪያው ኢኤስ ሴቲፍ ድል ቀንቶታል፡፡
ኦሞዱሩማን በሚገኘው የአል ሂላል ስታዲየም አል አሃሊ ትሪፖሊን ያስተናገደው የ2015 ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ግማሽ ተፋላሚ አል ሂላል በሙዳሂቲር ኤል ጣይብ ካሬካ ሁለት ግቦች 2-1 ቢያሸንፍም ከውድድር ተሰናብቷል፡፡ የትሪፖሊው ክለብ ከሳምንት በፊት ቱኒዚያ ላይ ሂላልን 1-0 ያሸነፈ ሲሆን በመልሱ ጨዋታ መሃመድ አል ኖዲ በመጀመሪያ አጋማሽ ያስቆጠራት ግብ የሊቢያው ክለብ ከሜዳው ውጪ ባስቆጠራት ግብ ታግዞ ጣፋጭ የሆነ ድምር ውጤት እንዲያስመዘገብ አድርጎታል፡፡
በጃ አልጄሪያ ላይ በተደረገ ጨዋታ መውሊዲያ ቤጃ የቱኒዚያ ሻምፒዮኑ ክለብ አፍሪካን ባጠቃላይ ውጤት 2-1 በመርታት ወደ ተከታዩ ዙር ማለፍ ችሏል፡፡ የቢጃን ሁለት ግቦች በሁለተኛው አጋማሽ ሴኔጋላዊው አጥቂ ንዶዬ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም የአልጄሪያ እና ቻድ ጥምር ዜግነት ያለው ቤቶራንግል ከመረብ አዋህደዋል፡፡ የ2014 የቻምፒየንስ ሊግ ባለድሉ አልጄሪያው ኢኤስ ሴቲፍ የኮንጎ ብራዛቪሉን ኤቷል ዲ ኮንጎን በሴቲፍ ከተማ 4-2 ረትቷል፡፡ ከሴቲፍ ግቦች የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተወላጁ ዳጎሎ በጨዋታው ላይ ሶስት ግቦች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሲሰራ ቀሪዋን ግብ አሞክሬን ከመረብ አዋህዷል፡፡ የኮትዲቯሩ አሴክ ሚሞሳ ከደቡብ አፍሪካው ካይዘር ቼፍስ ጋር ያለግብ 0-0 በመለያየቱ በድምር ውጤት ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፍ ችሏል፡፡ የዛምቢያው ዜስኮ ዩናይትድ በሆሮያ ኮናክሬ 2-0 ተሸንፎም ወደ ቀጣዩ ዙር የማጣሪያ ዙር አልፏል፡፡ በጨዋታው ላይ ዜስኮ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ሲወጣበት የጨዋታው ዳኛ የጨዋታው መጠናቀቂ ላይ የተጨመረው ደቂቃ 6 ቢሆንም ለ12 ደቂቃዎች ጨዋታው እንዲቀጥል ማድረጋቸው ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ዜስኮ ዩናይትድ ወደ ኮናክሬ የተጓዘው ዋና አሰልጣኙን ጆርጅ ላዋንዳሚና ሳይዝ ነበር፡፡
ግብፅ፣ አልጄሪያ እና ዲ.ሪ. ኮንጎ በቻምፒየንስ ሊጉ እየተሳተፉ የሚገኙት ሁሉም ክለቦቻቸው ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል፡፡ አልጄሪያ እና ግብፅ በኮንፌድሬሽንስ ካፑም በተመሳሳይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሁሉም ክለቦቻቸው ወደ ቀጣዩ አልፈዋል፡፡
የዕሁድ ውጤቶች
ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) 1-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ (ኢትዮጵያ) [3-2]
አል ሂላል (ሱዳን) 2-1 አልሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) [2-2 አልአህሊ ትሪፖሊ አላፊ ሆኗል]
ኮተን ስፖርት (ካሜሮን) 1-0 ስታደ ማሊያን (ማሊ) [1-2]
ሆሮያ ኮናክሬ (ጊኒ) 2-0 ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) [3-4]
አሴክ ሚሞሳ (ኮትዲቯር) 0-0 ካይዘር ቼፍስ (ደቡብ አፍሪካ) [1-0]
መውሊዲያ ቤጃ (አልጄሪያ) 2-0 ክለብ አፍሪካ (ቱኒዚያ) [2-1]
ኢኤስ ሴቲፍ (አልጄሪያ) 4-2 ኤቷል ዲ ኮንጎ (ኮንጎ ብራዛቪል) [5-3]
ክለብ ፌሮቪያሪዮ ዲ ማፑቶ (ሞዛምቢክ) 1-1 ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) [1-2]
የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች
ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)
ዋይዳድ ካዛብላንካ (ሞሮኮ) ከ ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)
ኤል ሜሪክ (ሱዳን) ከ ኢኤስ ሴቲፍ (አልጄሪያ)
ስታደ ማሊያን (ማሊ) ከ ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)
ያንጋ አፍሪካ (ታንዛኒያ) ከ አል አሃሊ (ግብፅ)
ዛማሌክ (ግብፅ) ከ መውሊዲያ ቤጃ (አልጄሪያ)
አሴክ ሚሞሳ (ኮትዲቯር) ከ አልሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ)
ኢኒምባ (ናይጄሪያ) ከ ኤቷል ደ ሳህል (ቱኒዚያ)
*የ2ኛ ዙር 8 አሸናፊዎች ወደ ምድብ ድልድል ሲያመሩ ተሸናፊዎች ደግሞ ወደ ኮንፌዴሬሽንስ ካፕ 2ኛ ዙር ያመራሉ፡፡
ፎቶ – አል ሂላል ከ አል አሃሊ ትሪፖሊ (ከሂላል የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ)