ኡመድ ኡኩሪ ግብ ባስቆጠረበት ጨዋታ ኢኤንፒፒአይ ወደ ቀጣዩ የኮንፌዴሬሽንስ ካፕ ዙር አልፏል

በ2006 ኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽንስ ካፕ የግብፁ ኢኤንፒፒአይ የኮትዲቯር ተወካዩ አፍሪካ ስፖርትስ 4-1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ከሳምንት በፊት አቢጃን ላይ ያደረጉት ጨዋታ በኢኤንፒፒአይ የ2-0 አሸነፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን በመልሱም ጨዋታ ኢኤንፒፒአይ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል፡፡

በጨዋታው ላይ ለ52 ደቂቃዎች ተሰልፎ የተጫወተው ኡመድ ኡኩሪ ለሁለት ግቦች መገኘት ቁልፋ ሚናን ተጫውቷል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ የአፍሪካ ስፖርት ተከላካይ ኡመድ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ኢብራሂም ያህያ ሲያስቆጥር የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት የኢኤንፒፒአይ ተጫዋች በግንባሩ የገጫትን ኳስ ተጠቅሞ ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ኡመድ ሁለተኛዋን ግብ አክሏል፡፡ ይህች ጎል በዓመቱ መጀመሪያ ኢኤንፒፒአይን ለተቀላቀለው ኡመድ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ግብ ነች፡፡ አፍሪካ ስፖርትስ በትራኦሬ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ውጤቱን ቢያጠቡም ካሜሮናዊው ላማ ኮሊን እና ዋኤል ፋራጅ ለኢኤንፒፒአይ ተጨማሪ ግቦች በማከል የአጠቃላይ ውጤቱን ወደ 6-1 አድርሰውታል፡፡ ኢኤንፒፒአይ ሌላኛውን የግብፅ ክለብ ምስር አል ማቃሳን ተከትሎ ሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ተቀላቅሏል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *