‹‹ የምንፈልገውን ውጤት ባናሳካም ተጫዋቾቻችን ላሳዩት ተጋድሎ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ›› ዘሪሁን ሸንገታ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሉቡምባሺ ላይ በቲፒ ማዜምቤ 1-0 መሸነፉን ተከትሎ በድምር ውጤት 3-2 ተሸንፎ ከቻምፒዮንስ ሊጉ 1ኛ ዙር ተሰናብቷል፡፡ ከጨዋታው በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገረቻቸው ረዳት አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንጋታ እና የጨዋታው አምበል አዳነ ግርማ በእለቱ የነበረው ዳኝነት ውጤቱ ላይ ተጽእኖ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ የሁለቱን አስቴየት አጠር አድርገን እንዲህ አሰናድተነዋል፡-

‹‹ ውጤት ባናሳካም ተጫዋቾቻችን ላሳዩት ተጋድሎ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ›› ዘሪሁን ሸንገታ ‹‹ ለተጫዋቾቻችን በልምምድ ቦታ የሰጠናቸውን የቤት ስራ በመዳ ላይ ተግብረዋል፡፡ በጨዋታው ላይም ጥሩ መንቀሳቀስ ችለናል፡፡ ምክንያት ለማቅረብ ሳይሆን በዳኝነት ላይ የነበረው ውሳኔ ውጤታችን ላይ ተጽእኖ ፈጥሮብናል፡፡ በአጠቃላይ የቲፒ ማዜምቤን ደረጃ መዘንጋት የለብንም፡፡ ተጫዋቾቹ ያንን ተቋቁመው በሜዳ ላይ ላሳዩት ተጋድሎ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ‹‹ ከዚህ ውድድር ብዙ ተምረናል፡፡ አቅማችን የት ጋር እንዳለም አይተናል፡፡ ለቀጣዩ አመት ጠንክረን ለመቅረብ ከወዲሁ የቤት ስራችንን መስራት እንጀምራለን፡፡››

‹‹ ባይሳካልንም ጨዋታውን በማሸነፍ ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት ጥረን ነበር ›› አዳነ ግርማ

‹‹በጨዋታው ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ስናጠቃም ስንከላከልም በህብረት ነበር፡፡ በዳኝነት ላይ የደረሰብን በደል ግን ጨዋታችንን አበላሽቶብናል፡፡ ጨዋታው ገና ሳይጀምር ነበር ኦዶንካራ ልብስ እንዲቀይር በመንገር እንዲረበሽ ሲያደርገው የነበረው፡፡ በጨዋታው እንቅስቃሴም ላይም ዳኛው ፊሽካ በማብዛት ተረጋግተን እንዳንጫወት አድርጎናል፡፡ ‹‹በጨዋታው የምንችለውን አድርገናል፡፡ ደጋፊዎቻችንም በአካል ባይኖሩም በመንፈስ ከጎናችን እንደነበሩ በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች ሲገልፁልን ነበር፡፡ ባይሳካልንም ጨዋታውን በማሸነፍ እነሱን ለማስደሰት ጥረን ነበር፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተመለስን በኋላ ቀሪዎቹ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ውጤት በማስመዝገብና ዋንጫውን በማንሳት ደጋፊዎቻችንን እንክሳለን፡፡››

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *