የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታዎች ትላንት ተጀምረዋል፡፡ የካይሮ ሃያሎቹ አል አሃሊ እና ዛማሌክ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፉ የሞሮኮው ሻምፒዮን ዋይዳድ ካዛብላንካ ማዳካስካር ላይ ሽንፈት ቢ ጥመውም በአጠቃላይ ውጤት ወደ ሁለተኛ ዙር አልፏል፡፡ ካይሮ ላይ የአንጎላውን ሬክሬቲቮ ዲ ሊቦሎን ያስተናገደው አል አሃሊ 2-0 አሸንፏል፡፡ የቀዮቹን የድል ግቦች በጨዋታው ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ረመዳን ሶብሂ እና በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ የሳውዲ አረቢያውን አል ሸባብ ለቆ አሃሊን የተቀላቀለው ጋናዊው አጥቂ ጆን አንቲው አስቆጥረዋል፡፡ ፡በፔትሮስፖርት ስታዲየም በተደረገ ሌላ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ዛማሌክ የካሜሮኑን ዩኒየን ዱዋላን 2-0 በመርታት ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል፡፡ የዛማሌክን ግቦች መሃሙድ ካራባ እና ዛምቢያዊውን አጥቂ ኢማኑኤል ማዩካ በሁለተኛው አጋማሽ ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አህመድ ቶፊቅ ከመረብ አዋህደዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከሜዳው ውጪ ፖርት ኑዌር ላይ ከኮንጎ ብራዛቪሉ ኤሲ ሊዮፖርድን ጋር 1-1 በመለያየት በአጠቃላይ ውጤት 3-1 በማሸነፍ ሁለተኛው ዙር አልፏል፡፡
ኢትዮጵያዊው የመሃል ዳኛ ሃይለየሱስ ባዘዘው በመራው ጨዋታ የብሩንዲው ቪታሎ በሳሲሪ ናሂማና እና ላውዲት ማቩጎ ግቦች የናይጄሪያውን ኢኒየምባን 2-1 አሸንፏል፡፡ ኤቹክዉ ኤቤንግቡ ኢኒየምባን ማለፍ ያረጋገጠች ግብ በመጀመሪያው አጋማሽ በስሙ አስመዝግቧል፡፡ የካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊው ኤቷል ደ ሳህል፣ ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ ኤል ሜሪክ እና ያንጋ አፍሪካ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሌሎች ክለቦች ናቸው፡፡ ሻምፒዮንስ ሊጉ አሁንም በሰሜን አፍሪካ ክለቦች የበላይነት ስር ያለ ይመስላል፡፡ አብዛኛው ጊዜ ከሰሜን አፍሪካ የሚመጡ ክለቦች ውድድሩን በተከታታይ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ከ2004 ወዲህ ከቲፒ ማዜምቤ እና ኢኒየምባ ውጪ ቻምፒየንስ ሊጉን ያሸነፉት የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ናቸው፡፡
የቅዳሜ የአንደኛ ዙር ውጤቶች፡-
ሲኤንፒኤስ ስፖርትስ 2-1 ዋይዳድ ካዛብላንካ (ሞሮኮ) (3-6)
ኤሲ ሊዮፓርድስ (ኮንጎ ብራዛቪል) 1-1 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) (1-3)
አል አሃሊ (ግብፅ) 2-0 ሬክሬቲቮ ዲ ሊቦሎ (አንጎላ) (2-0)
ያንጋ አፍሪካ (ታንዛኒያ) 1-1 ኤፒአር (ሩዋንዳ) (3-2)
ኤቷል ደ ሳህል (ቱኒዚያ) 2-0 ኢሲ ኮብሪካ (ሞሮኮ) (3-1)
ቪታሎ (ቡሩንዲ) 2-1 ኢኒየምባ (ናይጄሪያ) (3-6)
ኤል ሜሪክ (ሱዳን) 1-0 ዋሪ ዎልቭስ (ናይጄሪያ) (2-0)
ዛማሌክ (ግብፅ) 2-0 ዩኒየን ዱዋላ (ካሜሮን) (3-0)
የአንደኛው ዙር ቀሪ 8 የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ የኮንጎው ቲፒ ማዜምቤን ከሜዳው ውጪ ይገጥማል፡፡ የዛሬ ጨዋታዎች የሚከተሉት ናቸው:-
*ፎቶ – ረመዳን ሶብሂ (ከአል አሃሊ የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ)