በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ቲፒ ማዜምቤ በስታደ ቲፒ ማዜምቤ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል፡፡ 18 ተጫዋቾችን ይዞ ሀሙስ እለት ወደ ሉቡምባሺ ያቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ያስመዘገበውን የአቻ ውጤት በመቀልበስ ወደ ተከታዪ ዙር ለማለፍ በባህርዳር የሰሯቸውን ስህተቶች ላለመድገም መጠንቀቅ እንደሚገባ በሃይሉ አሰፋ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡
” እንደነበረን ጥሩ እንቅስቃሴ በሜዳችን ባደረግነው ጨዋታ ማሸነፍ ነበረብን ፡፡ እግርኳስ በታሪክ ሳይሆን አሁን ባለህ ወቅታዊ አቋም የሚገለፀው፡፡ ወቅታዊ አቋምህ ጥሩ ከሆነ የማታሸንፍበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ እዚህ የተሳሳትናቸውን ስህተቶች ላለመድገም ተጠንቅቀን ከሜዳችን ውጪ የተሻለ ተንቀሳቅሰን ውጤቱን ለመቀልበስ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ ” ብሏል፡፡
በባህርዳሩ ፍልሚያ ከርቀት ባስቆጠረው ግሩም ግብ የከፈተው በሃይሉ በቻምፒዮንስ ሊጉ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ቡድኖችን ማሸነፍ እንደሚቻል ከ2009 በኀላ በቻምፒዮንስ ሊጉ በሜዳው ተሸንፎ የማያውቀው ቲፒ ማዜምቤን ለመርታት እየተዘጋጁ እንደሆነ ገልጿል፡፡ “በስማቸው አነስተኛ የሆኑ ክለቦች በቻምፒየንስ ሊጉ የተሻለ ርቀት ሲጓዙ አይተናል፡፡ ታሪክ ለመስራት ሁሉም ተጫዋች በፍላጎት ነው እየሰራ የሚገኘው፡፡ ” ሲል ታሪክ የመስራት ፍላጎታቸውን ገልጿል፡፡ የመስመር አማካዩ በመጨረሻም ቲፒ ማዜምቤን እንደ ትልቅ ክለብነቱ አክብሮት እንደሚሰጡት ተናግሯል፡፡ ” እኛ ሳንሆን ሚድያው ቲፒ ማዜምቤን አግዝፎት ነበር፡፡ እኛ ለማንኛውም ቡድን ከበሬታ አለን፡፡ ቲፒ ማዜምቤ የወቅቱ የቻምፒየንስ ሊግ እና ሱፐር ካፍ አሸናፊ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለክለቡ ከፍተኛ ግምት እንዲሰጠው አድርጓታል፡፡ ” ሲል አጠቃሏል፡፡