[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ14ኛ የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸው ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች የመጨረሻው የፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 በትጥቆች የላቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሀገራችን የእግርኳስ ክለቦች ታሪክ አንጋፋ የሆነው እና ለ14 ያህል ጊዜያት የሊጉ ባለክብር ቅዱስ ጊዮርጊስ በትጥቅ ረገድ ታላቅነቱን በሚያስመሰክር መልኩ ከሌሎች ክለቦች በረጅም ርቀት ልቆ ተቀምጧል።
ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ይፋዊ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት “ማክሮን” ከተሰኘው እና መቀመጫውን በጣሊያን ካደረገው የስፖርት ትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ያለው ቡድኑ በንድፍ (Design) ሆነ በጥራት ደረጃቸው የተሻሉ የስፖርት አልባሳትን ማለትም የመጫወቻ መለያዎች ፣ ቱታዎች ከመጠቀም ባለፈ የጉዞ ፣ የመመገቢያ ሆነ ሌሎች ጥራታቸውን የጠበቁ እና በተጫዋቾች የመለያ ቁጥር ተለይተው በቀለም አማራጮች የተሰሩ ትጥቆችን ጥቅም ላይ ሲያውሉ እየተመለከትን እንገኛለን።
እንደ አንጋፋነቱ በብዙ መስኮች ለሌሎች ክለቦች ምሳሌ መሆን የሚገባው ቡድኑ የትጥቅ አቅራቢዎችን እያሰባጠሩ ክለባዊ ማንነትን ያልተላበሱ በዘፈቀደ ከገበያ የሚገዙ ትጥቆችን እየተጠቀሙ ለሚገኙት አብዛኛዎቹ የሀገራችን ክለቦች ተምሳሌት የሚሆን ተግባርን እየፈፀመ ይገኛል።
👉 የተዘበራረቀው የ”ፎንት” መጠን
ሊጉ ከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አንስቶ የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ በአንድ ወቅት ለሀገራችን የእግርኳስ ቤተሰብ ሩቅ የነበሩት በመለያዎች በስተጀርባ የተጫዋቾች ስሞች ታትመው መመልከት ጀምረናል።
ታድያ በዚህ ሂደት በተለይ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ኩባንያ የሆነው “ጎፈሬ” በስፋት የመለያ አቅርቦት ድርሻውን መያዙን ተከትሎ የሚታይ እምርታን እያየን ብንገኝም እንደ ጅምር መጠነኛ ክፍተቶችን እየተመለከትን እንገኛለን።
ለአብነትም ከተጫዋቾች መለያ በስተጀርባ የምንመለከታቸው የተጫዋቾች ስም የፊደላት መጠን በአንዳንዶቹ ላይ ከልክ በላይ ገዝፈው በሌሎች ላይ ደግሞ በተመጣጣኝ መልኩ ተፅፈው እየተመለከትን እንገኛለን ፤ ለማሳያነትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻን የገጠሙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተጠቀሙት ሁለተኛ ተመራጭ መለያ ላይ ስማቸው በጥቂት ሆሄያት በሚፃፉት እንደነ “BAYE” ዓይነት ስሞች በጣም ከፍ ብለው ተፅፈው የተመለከትን ሲሆን በመጠኑም ቢሆን በርከት ባሉ ሆሄያት የሚፃፉ እንደነ “ABEBAYEHU” ዓይነት ስሞች ደግሞ ተመጣጣኝ በሆነ የፎንት መጠን ሲፃፉ ተመልክተናል።
በመሆኑም እንደ ሊግ በመሰል የፎንት ፣ የቀለም እና ሌሎች መዘርዝሮች ላይ በግልፅ የተቀመጠ ድንጋጌ ባይኖርም አምራቹ ድርጅት መሰል ልዩነቶችን ለማስቀረት በመለያዎች ላይ የሚሰፍሩ ተጫዋቾች ስሞች መጠን ግን ወጥ የሆነ እና ለእይታ በማያስቸግር መልኩ የተመጣጠነ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ ይገባል።
👉 ፍፁም ቅጣት ምቶች የበዙበት ሳምንት
በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ሰባት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ተመልክተናል።
ከተመለከትናቸው ሰባት ፍፁም ቅጣት ምቶች በሁለት ጨዋታዎች የተሰጡ ሲሆን በጨዋታ ሳምንቱ አነጋጋሪ በነበረው የሀዋሳ ከተማ እና መከላከያ ጨዋታ አምስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሲያሳየን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታዎች እንዲሁ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የተመለከትንበት ጨዋታ ነበር።
ከተሰጡት ሰባት የፍፁም ቅጣት ምቶች አምስቱ ወደ ግብነት ሲቀየሩ ሁለቱ ደግሞ በግብ ጠባቂዎች መክነዋል።
👉 ኖህ ደሳለኝ ተዘክሯል
በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ተካፋይ ለሆነው ቢሾፍቱ ከተማ በመሀል ተከላካይ ስፍራ ይጫወት የነበረው ኖህ ደሳለኝ ከቀናት በፊት በተሽከርካሪ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ አይዘነጋም።
ህልፈቱን ተከትሎ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ካደረጉት ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ የወላይታ ድቻ የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾች የተጫዋቹ ምስል ያረፈበትን ባነርን በማሰራት ተጫዋቹን የዘከሩ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ከወልቂጤ ካደረጉት ጨዋታ መጀመር አስቀድሞም የሁለቱ ቡድኖች አምበሎች የተጫዋቹ ምስል ያረፈበትን ባነር ይዘው በመግባት አስበውታል።
በተመሳሳይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንዲሁ ህይወቱ ያለፈውን የሰንዳፋ በኬ አጥቂ የነበረውን ታምራት ባልቻን ህልፈት ተከትሎ የሰበታ ከተማ ተጫዋቾች በተመሳሳይ ባነር አሰርተው የማስታወሻ ፎቶ መነሳታቸው አይዘነጋም።