[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 12ኛ ሳምንት ትናንት እና ዛሬ ተደርገዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ቡራዩ ከተማ እና ነቀምቴ ከተማም በመሪነታቸው ቀጥለዋል።
ምድብ ሀ
ጋሞ ጨንቻን ከአምቦ ከተማ ያገናኘው የትናንት 4፡00 ጨዋታ በአምቦ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ኢብሳ ጥላሁን በ73ኛው ደቂቃ የአምቦን ብቸኛ ግብ ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን በግርጌው የሚገኘው አምቦ ደረጃውን ባያሻሽልም ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ነፍስ የዘራበትን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክቷል።
በመቀጠል የተደረገው የባቱ ከተማ እና ጌዴኦ ዲላ ጨዋታም በተመሳሳይ ውጤት በጌዴኦ ዲላ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የዲላን ብቸኛ የድል ግብ የተቆጠረችው በሙሉዓለም በየነ አማካኝነት በ46ኛው ደቂቃ ነው።
10፡00 ላይ የምድቡ መሪ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ገላን ከተማን ገጥሞ 3-1 በማሸነፍ በመሪነት ቀጥሏል። ኢብራሂም ከድር በ16ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅታት ምት ቀዳሚዋን ጎል ሲያስቆጥር ከእረፍት በኋላ አቤል ሀብታሙ እና ፀጋ ደርቤ አከታትለው ከመረብ አገናኝተዋል። በጭማሪው ሰዓት የላንን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው በሱፍቃድ ነጋሽ ነው። ድሉን ተከትሎ ኤሌክትሪክ መሪነቱን በ27 ነጥቦች አስቀጥሏል።
ዛሬ የምድቡ ጨዋታዎች ቀጥለው በ8፡00 ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ነጌሌ አርሲ ሻሸመኔ ከተማን 3-2 አሸንፏል። ምስጋና ግርማ ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ባስቆጠረው ጎል አርሲዎች ቀዳሚ ሲሆኑ የቀድሞ የሲዳማ እና አዳማ ተጫዋች ፀጋዬ ባልቻ ሻሸመኔን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር። ሆኖም ከእረፍት በኋላ ጠንክረው የቀረቡት አርሲዎች በምስጋና ግርማ እና ሴፍ ተካልኝ ተጨማሪ ጎሎች አሸንፈው መውጣት ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎም ኬሌክትሪክ ያላቸውን የአንድ ነጥብ ልዩነት አስጠብቀው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ተከታታይ ድል አስመዝግቦ በጥሩ አቋም ላይ የነበረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀላባ ከተማ 1-0 ሽንፈት አስተናግዷል። ሀላባ ከተማ ድል አስመዝግቦ ደረጃውን እንዲያሻሽል የረዳችውን ግብ ያስቆጠረው አቡሽ ደርቤ ነው።
ምድብ ለ
ማክሰኞ በ4:00 ላይ ኮልፊ ቀራንዮ እና ለገጣፎ ለገዳዲን ያገናኘው ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል። ቡታጅራ ከተማን በመልቀቅ የኮልፊ ቀራንዮ አሰልጣንነትን የተረከቡት አሰልጣኝ መሳይ ቡድን ከባለፈው የቡራዩ ሽንፈት በመጠኑ ሲያገግም በተከታታይ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ለገጣፎ ለገዳዲም በሰንጠረዡ አናት ፉክክር ተጠቃሚ የሚሆንበትን ተደጋጋሚ እድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።
ቂርቆስ ክ/ከተማን ከ መሪው ቡራዩ ከተማ ያገናኘው የ8፡00 ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። የምድቡ መሪ የሆነው ቡራዩ ከተማ እንዲሁም የምድቡ ግርጊ ላይ የሚገኘው ቂርቆስ ክ/ከተማ ያገናኘ ጨዋታ እእደመሆኑ ከፍተኛው ግምት ለቡራዩ ከተማ ቢሰጥም አዲሱ የቂርቆስ ክ/ከተማ አሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ መሪውን ነጥብ አስጥለውታል።
በ10:00 ላይ በምድቡ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶ የነበረው ስልጤ ወራቤን ከ ቡታጅራ ያገናኘው ጨዋታ በቡታጅራ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል ። ከአሰልጣኝ መሳይ ጋር የተለያያው ቡታጅራ ከተማ በምትካቸው አሰልጣኝ ጥላሁን ሙሉጌታን ተክተዋል። አሰልጣኝ ጥላሁን ባደረጉት ሶስት ጨዋታ ባለመሸነፍ ወደ መሪዎቹ የሚደርጉትን ግስጋሴ አጠናክረዋል። ወንድማገኝ አብሬ በሁለተኛው ደቂቃ እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ በጋሻው ክንዴ ለቡታጅራ ግብ ያስቆጠሩ ተጫዎቾች ሲሆኑ ተጋጣሚያቸው ስልጤ ወራቤ በ79ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ሳዲቅ ሲቾ ግብ አስቆጥሯል።
በዘሬው ዕለት የምድቡ ጨዋታዎች ቀጥለው 8፡00 ላይ ካፋ ቡና ሸዒንሺቾን 2-1 አሸነፍፏል። ድራማዊ ክስተት ያስመለከተው የሁለቱ ጫዋታ ገና በጊዜ በ4ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ከፋቡና በዮሐንስ ሐይሶ ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ከፋ ቡናዎች በ66ኛው ደቂቃ ድልነሳው ሽታይ ባስቆጠረባቸው ግብ አቻ ሆኑ ቢቆይም የእለቱ ዳኛ ፊሽካ እየተጠበቀ ባለበት ሳዓት አጥቂው ይበልጣል ኤዶም ባስቆጠራት ግብ ከፋ ቡና 2-1 ማሸነፍ ችሏል።
በምድቡ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ አሰልጣኝ መሀመድ ኑርን ያመጣው ቤንች ማጂ ቡና ከ ሰንዳፋ ቤኬ ያገናኘው ጨዋታ ሲሆን ቤንጂ ማጂ ቡና 2-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪዎቹ እጅግ ተጠግቶል። የመጀመሪያው አጋማሽ መጠነቀቂያ ጭማሪ ሳዓት ላይ ላይ ሀብታሙ ረጋሳ አስቆጥሮ ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ ከእረፍት መልስ በድጋሚ ማበብ የጀመረው ወንድማገኝ ኬራ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።
ምድብ ሐ
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እየተደረገ በሚገኘው የምድብ ሐ ውድድር በዚህ ሳምንትም ትኩረት ሳቢ ውጤቶች ተመዝግበዋል። 10፡00 ላይ ሀምበሪቾን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን ጠንካራ ፉክክር ከአምበሪቾ ገጥሞት ጨዋታውን ያለ ጎል አጠናቋል።
8፡00 ላይም በተመሳሳይ ዘንድሮ መጥፎ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው የካ ክፍለከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።
ማክሰኞ ንጋት ላይ የተደረገው የአቃቂ ቃሊቲ እና ፌዴራል ፖሊስ ጨዋታ በፌዴራል ፖሊስ 3-1 አሸናፊነት ተገባዷል። ከአሸናፊነት ርቀው የነበሩት ፖሊሶች በ22ኛው ደቂቃ ላይ ቻላቸው ቤዛ አስቆጥሮ ቀዳሚ ቢደርግም የአቃቂ ቃሊቲ ሲሳይ ጥላሁን በ35ኛው ደቂቃ አቻ ማድረግ ችሏል። ከእረፍት መልስ ፌዴራል ፖሊሶች በ48ኛው ደቂቃ አንተነህ ተሻገር እና በ79ኛው ደቂቃ እሱባለሁ ፍቅሬ ግቦች አሸንፈው ወጥተዋል።
ትናንት መድን ከ ሀምበሪቾ ነጥብ መጋራቱን ተከትሎ ልዩነቱን የማስፋት እድል ይዞ የገባው ነቀምቴ ከተማ እድሉን በአግባቡ ተጠቅሞ ጅማ አባ ቡናን 1-0 በማሸፍ ልዩነቱን ወደ ሦስት ነጥብ አስፍቷል። ነቀምቴ ከተማ ጅማ አባቡናን በ33ኛው ደቂቃ ጌታሁን ባፋ ባገባት ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።
የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ሶዶ እና ጉለሌ ክ/ከተማ ያገናኘው ሲሆን 1-1 በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ለጉለሌ ሄኖክ ሞላ በ28ኛው ደቂቃ ሲስቆጥር ለወላይታ ሶዶ 59ኛው ደቂቃ አላዛር ፋሲካ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሯል።