[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ለአስራ አምስት የጨዋታ ሳምንታት የዘለቀው የ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር የመጀመሪያ ዙር ውድድር ትናንት ፍፃሜውን አግኝቷል። እኛም በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸው ትኩረት የሳቡ ክለቦች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮችን በመጀመሪያው ፅሁፋችን ለመዳሰስ ሞክረናል።
ፋሲልን የመሰለው ፋሲል ከነማ
የመጀመሪያ ዙሩን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባጠናቀቀው ሊጉ የዐምና አሸናፊዎቹ ፋሲል ከነማዎች ሁለት መልክ የነበረውን የመጀመሪያ ዙር ጉዟቸውን በሁለተኝነት ማጠናቀቅ ችለዋል። የዙሩ የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት በነበረው የመጨረሻው የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ የተመለከትነው የቡድኑ እንቅስቃሴን ሁለተኛው ዙር ማስቀጠል ከቻሉ በብዙ መልኩ ደጋፊዎች ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነበር።
በሦስት ተከታታይ ድሎች የውድድር ዘመኑን የጀመረው ፋሲል በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያውን ሽንፈት ካስተናገደበት አራተኛ የጨዋታ ስምንት እስከ ስድስተኛ ሳምንት ድረስ የመጀመሪያውን መጠነኛ ቀውስ (Mini Crisis) ያስተናገደ ሲሆን በሰባተኛ የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናን ረምርሞ በቀጣይ ሦስት ጨዋታዎች አዎንታዊ ውጤት በማስመዝገብ የተመለሰ ቢመስልም በአስረኛ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ያስተናገዱት አስደንጋጭ ሽንፈት ቡድኑ ላይ ዳግም ጥርጣሬዎች እንዲነሱ ያስገደደ ነበር።
በቀጣይ ጨዋታ ሰበታን አሸንፎ የተመለሰ ይመስል የነበረው ቡድኑ በአስራ ሦስተኛ ሳምንት ዳግም ሽንፈት ሲያስተናግድ በተከታታይ ግን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ አሳምነው ድሬዳዋ ከተማን የረቱበት እንቅስቃሴ በብዙ መልኩ በበጎነቱ የሚነሳ ነበር።
ከፍ ባለ ተነሳሽነት እና በላቀ የትጋት ደረጃ ላይ ሆነው ድሬዳዋ ከተማን የገጠሙት ፋሲል ከነማዎች ከወትሮዎቹ ጨዋታዎች በተሻለ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመለከተነው አንዱ ሌላኛው በጎ ነገር የፋሲል ከነማ የመሀል ለመሀል ጥቃቶች በጣሙን ተሻሽለው የመመልከታችን ነገር ነው። በመጀመሪያ አጋማሽ በነበረው የጨዋታ ሂደት 86% የሚሆኑት የፋሲል ጥቃቶች መነሻቸውን መሀል ለመሀል ማድረጋቸው ለወትሮው ዕድሎችን ለመፍጠር በመስመሮች በኩል በተለይም የበረከት ደስታን ተፅዕኖን ይፈልግ ለነበረው ቡድን በመልካምነቱ የሚነሳ ነው።
4-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ሌላኛው በጥሩነት የሚነሳው ጉዳይ ቡድኑ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ በጥራት የመጨረስ አፈፃፀማቸው በጣም የተሻሻለ ነበር።
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከ15 ጨዋታዎች በኋላ 12 ጨዋታዎችን አሸንፈው በሁለት ጨዋታ አቻ እንዲሁም በአንድ ጨዋታ ብቻ በመሸነፍ በ38 ነጥብ ሊጉን ይመሩ የነበሩት ፋሲሎች ዘንድሮ ግን 7 ጨዋታዎችን ብቻ አሸንፈው በአምስቱ አቻ እንዲሁም በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ተሸንፈው በ26 ነጥብ በ3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ተደጋጋሚ በሆነ መጠነኛ ቀውሶች ውስጥ እያለፈ የሚገኘው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ያሳዩትን ተስፋ ሰጪ ሂደት በሁለተኛው ዙር አጠናክረው ይቀርባሉ ወይ የሚለው ጉዳይ በጉጉት ይጠበቃል።
የድሬዳዋ ከተማ ችግር ምን ይሆን?
በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ ገናና ስም የነበራት ድሬዳዋ ከተማ አሁን ላይ በብዙ መልኩ በስፖርቱ ላይ ያላት ተፅዕኖ በጣሙን ተቀዛቅዞ ይታያል። በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማፍራትም ሆነ በጠንካራ ክለቦቿ ትታወቅ የነበረችው ድሬዳዋ አሁን ላይ በሊጉ ደረጃ እንኳን በጥቂት ተጫዋቾች እና በአንድ ክለብ እየተወከለች ትገኛለች።
ድሬዳዋ ከተማ ወደ ሊጉ ዳግም በ2009 ከተመለሰ ወዲህ በሊጉ ተፎካካሪ መሆን ይቅርና ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ላለመውረድ እየታገለ በስተመጨረሻም በሊጉ ቆይታውን ሲያረጋግጥ እየተመለከትን እንገኛለን። እርግጥ የዘንድሮው ውድድር ዘመን አጋማሹ ላይ ቢገኝም ከወዲሁ ዋና አሰልጣኙን አግዶ በጊዜያዊ አሰልጣኝ እየተመራ የሚገኘው ቡድኑ አሁናዊው አካሄዱ ስጋትን የሚያጭር ነው።
በድሬዳዋ ደረጃ ጠንካራ የእግርኳስ ታሪክ ላለው ከተማ የቡድኑ ያለፉት ዓመታት ውጤት እጅጉን አንገት የሚያስደፋ ነው። በእግርኳስ ተፎካካሪ ቡድንን ለመገንባት ከእግርኳስ ታሪክ በተከታታይ ዓመታት የሚሰሩ በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ያሉ ጉዳዮች ድምር ውጤት የቡድንን ውጤት ይወስናሉ። በጥቅሉ ግን በሀገራችን አውድ ከተፎካካሪ ቡድኖች በስተጀርባ ጠንካራ የእግር ኳስ አመራር፣ ፈርጣማ የፋይናንስ አቅም ፣ የተረጋጋ የቡድን ስብስብ ፣ ጠንካራ የደጋፊ መሰረት ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ልዩነት ፈጣሪ ምሰሶዎች ናቸው።
ታድያ በድሬዳዋ ከተማ ንባራዊ ሁኔታ ግን ከላይ የጠቀስናቸው ነገሮች ሙሉ ለሙሉ ባይባል እንኳ አመርቂ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብሎ ለመናገር የሚያበቃ ሁኔታ የለም። አንድ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ጉዳይ በአጠቃላይ በክለቡም ሆነ በአስተዳደሩ ዙርያ ያሉ አመራሮች ተፎካካሪ ቡድን የመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው ለዚህም የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በማቅረብ ረገድ የሚታሙ ባይሆንም ይህን እሳቤ በሚታይ ደረጃ ወደ ሜዳ ላይ ለማውረድ ግን ስለመቸገራቸው በግልፅ እየተመለከትን እንገኛለን።
በሊጉ በርከት ያሉ አሰልጣኞችን በመቀየር ሆነ የአዳዲስ አሰልጣኞች ቅጥርን ተከትሎ ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸውን ተጫዋቾችን በማዘዋወር በጣም ተቀያያሪ የቡድን ስብስብ ያለው ድሬዳዋ ምናልባት ከሌሎች ቡድኖች በተለየ መልኩ በክረምቱም ሆነ በአጋማሹ የቡድን ስብስባቸውን ለመቀየር ያላቸው ድፍረት በጣም የሚያስገርም ነው። ለአብነትም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ቡድኑ ሊጉ አዲስ አበባ ላይ ሲጀምር እና በመጨረሻው የሀዋሳ ውድድር የተጠቀመበትን የቡድን ስብስብ መመልከት በቂ ነው።
ምናልባት ይህ መለዋወጥ ክለቡ ለሚቀጥራቸው አሰልጣኞች ውጤታማነት በሚፈልጉት መጠን ድጋፍ ማድረጉን ማሳያ ነው በሚል መከራከር ቢቻልም ይህ ሂደት በየውድድር ዘመኑ የቡድኑ ወቅታዊ ግብ የሚሆነውን በሊጉ መቆየትን ከማረጋገጥ ባለፈ ቡድኑን በሚታይ መልኩ ፈቀቅ ሲያደርገው አልተመለከትንም።
እርግጥ ያልተረጋጋ ስብስብ ለድሬዳዋ ከተማ ብቻ የሚነሳ ጉዳይ አለመሆኑ ቢታወቅም ምናልባት የድሬዳዋን ለየት የሚያደርገው በእነዚህ ሁሉ መለዋወጦች ውስጥ ሁሌም ቢሆን በወራጅ ቀጠና ውስጥ ከመዳከር ያለፈ ውጤት ማስመዝገብ ያለመቻላቸው ጉዳይ ይነሳል።
በአሁኑ ሰዓት በሊጉ በ13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ዙሩን ያጠናቀቀው ቡድኑ አምና ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ብሎ 10ኛ መጨረስ ሲችል ከዚያ በፊት በነበሩት የውድድር ዘመናት 13ኛ (2012*) ፣12ኛ (2011)፣ 12ኛ (2010) ፣ 11ኛ (2009) በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል ፤ ይህም ከቡድኑ አመራሮች ሆነ ደጋፊዎች ፍላጎት ጋር ፍፁም የሚጣጣም አይደለም።
በመሆኑም ድሬዳዋ እስካሁን እየተመራበት የሚገኘው በአፍንጫ ስር ዕይታ የታጠረ አካሄድ ቡድኑን በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ እንዲዳክር ያስገደደው ሲሆን ታድያ ቡድኑ በመሰረታዊነት ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ሊመልሳቸው የሚገቡትን ሁለት ዓበይት ጥያቄዎች ናቸው።
አንደኛው እና መሰረታዊው ጉዳይ አሰልጣኞች በጥሩ የምልመላ ስርዓት ወደ ቡድን ማምጣት ከመጡም በኋላ ደግሞ ስራቸውን ከጣልቃ ገብነት በፀዳ መልኩ ሊሰሩበት የሚችሉበትን ከባቢ መፍጠር እንዲሁም በቂ ጊዜ መስጠት ከክለቡ ኃላፊዎች ይጠበቃል። ይህ ሳይሆን ግን በአጭር ጊዜ እሳቤ የእስካሁኑን አካሄድ ካስቀጠሉ የተለየ ውጤት መጠበቅ ከባድ ነው የሚሆነው።
ሌላኛው ጉዳይ እርግጥ በእግርኳስ ማንም ስፖርቱ የሚፈልገውን ነገር ማሟላት እስከቻለ ሁኔታዎች ሳይገድቡት በተለያዩ ክለቦች መጫወት እንደሚቻል ቢታመንም እንደ ድሬዳዋ ባሉ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ እግርኳስ አቅም ያላቸው ወጣቶችን በማፍራት የሚታወቅ ቀጠናን የሚወክል ቡድን አሁን ላይ በርካታ ተጫዋቾችን በዝውውር ከሌሎች አካባቢዎች በማምጣት ውጤታማ ለመሆን ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ አለመሆኑን ተከትሎ በርካታ የቡድኑ ደጋፊዎች ይህን ዕድል ‘የእኛ’ የሚሏቸው ወጣቶች አግኝተው መመልከትን ይሻሉ።
አሁን ላይ በስብስቡ ካሉ ወጣቶች ጀምሮ ምን ያህሉ በዚህ ደረጃ ለመጫወት ብቁ ናቸው ? የሚለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ የቡድኑ ደጋፊዎች ይህኛው ጥያቄን በቂ ምላሽ በመስጠት በተወሰነ መልኩ ውጤት ባይኖር እንኳን የቡድኑን ደጋፊዎች ከቡድኑ ጋር “በአንድ ገፅ” ለማቆየት ከመርዳቱ አንፃር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ከውጤት ማጣት ጋር እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ትኩረቱን ከከተማው ክለብ ላይ የነቀለውን የድሬዳዋ ደጋፊን ወደ ክለቡ ለመመለስ ከተማዋን የመሰለ ክለብ መገንባት የግድ ይላል። በመሆኑም ድሬዳዋ ከተማን የሚመጥን ተፎካካሪ ቡድን ለመገንባት በክለቡ ዙርያ የተሰባሰቡ አካላት በሙሉ ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ በጠቀስናቸውና በሌሎች ወሳኝ ችግሮች ላይ መፍትሄ በማበጀት ቡድኑን የተሻለ ለማድረግ በጋራ መስራት ካልቻሉ በየዓመቱ በስጋት የተሞላ የውድድር ዘመን ማሳለፋቸው አይቀሬ ነው።
ድንቅ የመከላከል ብቃት ያሳዩት ሀዋሳ ከተማዎች
በሰንጠረዡ አናት ቅዱስ ጊዮርጊስን በቅርብ ርቀት እየተከተሉ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ዙሩን ከመሪው በአራት ነጥብ ርቀው በሦስተኝነት ማጠናቀቅ ችለዋል። በጨዋታ ሳምንቱ አዳማ ከተማን የገጠመው ቡድኑ ገና በጊዜ ግብ ጠባቂያቸውን መሀመድ ሙንታሪን በቀይ ካርድ ሳቢያ አጥተው ከ70 ለሚልቁ የጨዋታ ደቂቃዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ግብ ሳያስተናግዱ ከአዳማ ከተማ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን ያጠናቀቁበት መንገድ በመልካምነቱ የሚወሰድ ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ግብ ጠባቂያቸውን በቀይ ካርድ ያጡት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ተተኪ ግብ ጠባቂ ለማስገባት ይበልጥ የመከላከል አጨዋታቸውን ሊያግዝ በሚችል መልኩ የማጥቃት ባህሪ ያለው ተጫዋችን ይቀንሳሉ ተብሎ ቢጠበቅም እሳቸው ግን ሳይጠበቅ የተከላካይ አማካዩ አብዱልባሲጥ ከማልን ከሜዳ በማስወጣት በምትኩ ግብ ጠባቂውን ዳግም ተፈራን ቀይረው አስገብተዋል።
በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር በተጫወቱባቸው ከ70 በላቁ የጨዋታ ደቂቃዎች በተለይ አዳማ ከተማዎች ጠንካራ ጎን የሆነውን ፈጣን አጥቂዎቻቸውን በተደጋጋሚ የማስሮጫ ክፍተቶችን እየፈለጉ ከተጋጣሚ ተከላካዮች ጀርባ ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረት እንዳይሳካ ለማድረግ ከሳጥናቸው አንፃር ርቀታቸውን ጠብቀው ለመከላከል ያደርጉት የነበረው ጥረት አስገራሚ የነበረ ሲሆን ከዚህም ባለፈ በጨዋታው በጥቅሉ በአስር ተጫዋቾች የነበራቸው የመከላከል አወቃቀር ድንቅ ነበር።
ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች ሊጉን ማሸነፍ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ከዓመታት በኋላ ወደ ሰንጠረዡ አናት ተጠግተው ሊጉን ስለማሸነፍ ማለም የጀመሩ ሲሆን ቡድኑ በጎዶሎ ተጫዋች ያሳዩት የጨዋታ እንቅስቃሴ ምናልባት ቡድኑ ዘንድሮ ለዋንጫ ከሚጫወቱ ቡድኖች አንዱ ስለመሆኑ ፍንጭ ሊሰጠን የሚችል አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።
በሰንጠረዡ አናት ከሚገኙ ቡድኖች አንፃር ከፍተኛ ቁጥር ያለው አስራ አራት ግቦችን ያስተናገደው ቡድን ይህን የመከላከል ጥንካሬ በሁለተኛው ዙር አሳድጎ የሚቀርብ ከሆነ ቡድኑ በእጅ ካለው የአጥቂ ተጫዋቾች ጥራት አንፃር በሊጉ በሁለተኛ ዙር ይበልጥ ተፎካካሪ ሆኖ መዝለቅ ይችላል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል አድርጓል
በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ከሀዲያ ሆሳዕና እና አርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኮቪድ በተፈተኑበት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን ከመመራት ተነስተው በማሸነፍ አጋማሹን በሦስት ነጥብ ልዩነት ከተከታያቸው ልቀው ለማጠናቀቅ በቅተዋል።
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠሙት ቡድኖች በተለያየ የጨዋታ መንገድ ውስጥ ቢሆንም የቅዱስ ጊዮርጊስ ሁነኛ የግብ ማስቆጠርያ አማራጭ የሆነውን ከተከላካይ ጀርባ አጥቂዎቻቸውን ለማስገባት ያላቸውን ውጥን እንዳይሰምር ለማድረግ ያደረጉት ጥረት የቅዱስ ጊዮርጊስን ማጥቃት የሠመረ እንዳይሆን ማድረግ ችለዋል።
እርግጥ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ካላቸው ባህሪ አንፃር ይህ መንገድ የተሻለ አዋጩ መንገድ መሆኑ ቢታመንም በተቃራኒው እነዚህን ክፍተቶችን የሚነፍግ ተጋጣሚ ሲያጋጥመው ቡድኑ ሌሎች አማራጭ የጨዋታ መንገዶች በጥራት ለመተግበር ሲቸገር እያስተዋልን እንገኛለን። ይህም በተለይ በሁለተኛው ዙር በሚኖሩ ጨዋታዎች ከእያንዳንዱ ጨዋታ የሚገኙ ነጥቦች ትልቅ ዋጋ በሚኖራቸው መፃኢ ወቅቶች የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚዎች ይበልጥ አለመሸነፍን ቅድሚያ ሰጥተው በሚጫወቱባቸው ጊዜያት ትልቅ ፈተና ሊጠብቀው እንደሚችል ይጠበቃል። እርግጥ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኮቪድ ምክንያት የነበራቸው የተጫዋቾች ምርጫ የተመናመነ ቢሆንም በጨዋታው በመጨረሻ 10 ደቂቃዎች በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ታግዘው አዲስ አበባ ከተማን 3-1 መርታት ቢችሉም በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ ግቡ ተጠግቶ ሲከላከል የነበረውን የአዲስ አበባ የመከላከል ውቅር ለመሰበር በጣሙን ተቸግረው ተመልከተናል። በመሆኑም ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ለሚጠብቀው ጠንከር ላለ ፈተና በዕረፍቱ ጊዜ ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል።
በዚህም ሂደት መሰረታዊው የሚሆነው ጉዳይ ቡድኑን የተሻለ ውጤት እያስገኘለት ባለው በዚህ የማጥቃት ሽግግር ጨዋታ ሆነ ቀጥተኝነት ይበልጥ አፈፃፀማቸውን ማሳደግ ሲሆን ከዚህም ባለፈ አማራጭ የማጥቂያ መንገዶች ማዘጋጀት የግድ ይላቸዋል።
ከክብደታቸው በላይ ቡጢ እየሰነዘሩ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች
የመጀመሪያ ዙር ሲጠናቀቅ ከተደረጉ አስራ አምስት ጨዋታዎች ዘጠኙን በማሸነፍ በሊጉ ቀዳሚው ቡድን ወላይታ ድቻ ሆኗል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከዚህ ቀደም ወላይታ ድቻ በተነፃፃሪነት ውጤታማ በነበሩባቸው ዘመናት ይታወቁ ወደ ነበሩበት መሰረታዊ የጨዋታ እሳቤያቸው ቡድኑን የመለሱት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በእጃቸው ካለው የስብስብ ጥራት አንፃር ከፍ ያለ ውጤትን አስመዝግበው በመጀመሪያው ዙር ማጠናቀቅ ችለዋል።
ቡድኑ ከጨዋታ ውበት ይልቅ ሜዳ ላይ ውጤት ይዞ የመውጣትን ተቀዳሚ አላማ በማንገብ በጥንቃቄ በመከላከል በቀጥተኛ ኳሶች እና በተወሰኑ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ከጨዋታዎች ውጤት ይዘው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል።
ዘጠነኛ ጨዋታቸውን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ማሸነፍ የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ካሸነፋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ውስጥ ሰባቱን በአንድ የግብ ልዩነት ብቻ ማሸነፋቸው ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ከጨዋታ ቁጥጥር ይልቅ ተጋጣሚን መሰላቸት ውስጥ በመክተት የሚያገኟቸውን ጥቂት አጋጣሚዎችን የሚጠቀም ቡድን ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
አሰልጣኙም ደጋግመው እንደተናገሩት የቡድናቸው የስብስብ ጥራት ጉዳይ በግልፅ የሚታይ ሲሆን ምናልባት በአጋማሹ የዝውውር መስኮት የተሻሉ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው መቀላቀል የሚችሉ ከሆነ በአሰልጣኙ ከተገለፀው በሊጉ የመቆየት ተቀዳሚ አላማ ተላቀው በሊጉ የተሻለን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ይችላሉ።