[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከቀናት በፊት የኋላ መስመር ተጫዋች ያስፈረመው መከላከያ አሁን ደግሞ አጥቂ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።
የካቲት 24 በተከፈተው የሁለተኛ ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው መከላከያ ከቀናቶች በፊት ተከላካዩ አሚኑ ነስሩን በ16 ወራት ኮንትራት ማስፈረሙን ዘግበን ነበር። ለሁለተኛው ዙር ውድድር ከሦስት ቀናት በፊት ቢሾፍቱ ላይ ዝግጅቱን የጀመረው ስብስቡ ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ የፊት መስመሩን ለማጠናከር ተጫዋች ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች አጥቂው እስራኤል እሸቱ ነው። ከሀዋሳ የታዳጊ ቡድን የተገኘው ይህ አጥቂ አራት ዓመታትን ለሀይቆቹ ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ወደ ሰበታ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ አምርቶ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። ተጫዋቹ ከሳምንታት በፊት ከሠራተኞቹ ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ አሁን አዲሱን ማረፊያው መከላከያ አድርጓል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተገኝቶም የ16 ወራት ኮንትራት ፈርሟል። ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በጣምራ በሊጉ ዝቅተኛ ግቦችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ክለቡ ዝውውሩን ተከትሎ ፊት መስመሩ እንደሚጠናከር ይጠበቃል።